Fana: At a Speed of Life!

350 ሺህ ዶላር በማሸሽ የተጠረጠረው ነጋዴ ፍርድ ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)350 ሺህ ዶላር በሕገ-ወጥ መንገድ አሽሽቷል ተብሎ የተጠረጠረው ነጋዴ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ነጋዴው ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ወደ ሀገር ውስጥ ይዤ የገባሁት ነው በሚል ሊያሸሽ ሲሞክር ነው ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር የዋለው ፡፡

ከትናንት በስቲያ በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ ሥም አቶ ሕይወት መልኩ ታደሰ እንደሚባልና በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ጉዳዩ መታየቱ ተገልጿል።

ተጠርጣሪው በጉሙሩክ ኮሚሽን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሚሰራ አንድ ሰራተኛ ጋር በመመሳጠር እ.ኤ.አ በ15/8/2019 ዓ.ም ምንም የጉዞ ታሪክ ሳይኖረው 350 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ይዤ የገባሁት ነው በማለት የጉሙሩክ ዲክላራሲዮን ሠነድ በመጠቀም በጉሙሩክ ሰራተኛ አማካኝነት ዲክሌር በማስደረግ ዶላሩን በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ በማሸሽ በአቋራጭ ለመበልፀግ በማሰብ በመንግስትና በህዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል መጠርጠሩን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

በዚህ መነሻ በተጠርጣሪው ላይ የ12 የሰው ምስክር ቃል ለመቀበል ፣በህገወጥ መንገድ የተመዘበረ የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ለምን አገልግሎት እንደዋለ ሙያዊ የምስክርነት ቃል ለመቀበል፣ ከተለያዩ ባንኮች እና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 52/2 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል መርማሪው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው ቀደም ብሎ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን በጥርጣሬ መነሻው የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

ተጠርጣሪው ከትናንት በስቲያ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ምሽት 3 ሰዓት ላይ በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሉን የጠቀሱት ጠበቃው ከተጠቀሰው ወንጀል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ሲሉ ተከራክረዋል።

በተጨማሪም የተጠርጣሪው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.