ባለፉት 5 ዓመታት ከ473 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል – አይ ኦ ኤም
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ከ473 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ዓለምአቀፉ የሥደተኞች ድርጅት አስታወቀ፡፡
ከኢትዮጵያ የሚነሱ ሥደተኞች አብዛኛውን ጊዜ መዳረሻቸው መካከለኛው ምሥራቅ ፣ አውሮፓ ወይም ደቡብ አፍሪካ እንደሆነም ነው መረጃው ያመላከተው፡፡
ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 2022 ባሉት አምስት ዓመታትም ከ473 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥደተኞች ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ አጋሮቼ ከሚላቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተመላሽ ሥደተኞችን ወደ ማኅበረሰባቸው ለመቀላቀል ፣ መልሶ ለማቋቋም እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱንም በመረጃው አስታውሷል፡፡
ዓለምአቀፉ የሥደተኞች ድርጅት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በራሳቸው ፈቃድ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ እና በየመን በተቀሰቀሰው ጦርነት አስገዳጅነት የተፈናቀሉ ሥደተኞችን ሲደግፍ መቆየቱንም ጠቁሟል፡፡