በሲዳማ ክልል በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እቀውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 177 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እውቅና ሰጠ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ የትምህርት ችግሮቻችንን ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ክልሉ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ክልሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ክልሉ ካስፈተናቸው ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከ3 በመቶ በታች ያህሉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባታቸውን ገልፀዋል ።
ዛሬ እውቅና ከተሰጣቸው 177 ተማሪዎች በተጨማሪ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 11 ተማሪዎች በሀገር አቀፍ የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ የተሳተፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
እንደክልል በሁሉም ቀበሌዎች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡
በመቅደስ አስፋው