ምርት በማከማቸት የዋጋ ንረት እንዲኖር በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የጤፍና የስንዴ ምርት በማከማቸት የዋጋ ንረት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ እና የዋጋ ማረጋጋት ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ጃንጥራር ዓባይ÷ የጤፍና የስንዴ ምርት ወደ ከተማዋ በበቂ ሁኔታ አለመግባቱን ተከትሎ በከተማዋ የተፈጠረውን የምርት እጥረትና የዋጋ መናር ለማረጋጋት አስተዳደሩ በጀት መድቦ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሎች በቂ የጤፍ ምርት ስለመኖሩም መረጃ መሰብሰቡን አቶ ጃንጥራር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም አስተዳደሩ የንግድ ስራ ዩኒየኖችን በማስተባበርና ከማኅበራት ጋር በማስተሳሰር ምርት ወደ ከተማዋ እንዲገባ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጤፍና የስንዴ ምርትን ወደ አዲስ አበባ በማስገባት ሂደት ላይ በኬላዎች አካባቢ በህገ ወጥ አካላት መስተጓጎሎች እንዳያጋጥሙ ከኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ጋር ስምምነት ተደርሷል ነው ያሉት፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ህጋዊ አሰራርን ተከትለው ዩኒየኖች ምርት ይዘው እንዲገቡ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር÷ በዛሬው ዕለት በግለሰቦች ደረጃ በቂ ምርት ወደ መርካቶ መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
ይህም የተከሰተውን የምርት እጥረት እንደሚቀንስ ነው የገለጹት፡፡
በሌላ በኩል ዛሬ በዘርፉ ላይ ነጋዴ ያልሆኑ ግለሰቦች በመጋዘን የጤፍ ምርት አከማችተው መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡
የምርት እጥረት እንዲኖር በህገወጥ መንገድ አከማችተው ዋጋ ጨምረው ለመሸጥ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በታሪክ አዱኛ