ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር እንደምታጠናክር ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር አጠናክር እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከቼክ ተቀዳሚ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጂሪ ኮዛክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ኢትዮጵያ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ገጸዋል፡፡
በተለያዩ የልማት ዘርፎች በተለይም የሙዝ ምርት ልማትን በደቡብ ኢትዮጵያ ለማሳደግ የቼክ ሪፐብሊክ መንግስት ያደረገውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡
የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተደረገውን የኢኮኖሚ መሻሻያ ተጠቅመው በተለያዩ ዘርፎች ማዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታማ እንደሚሆኑ አመልክተዋል፡፡
ሀገሪቱ ለኢትዮጵያ የምታደርገው የልማት ድጋፍ በዩክሬን ሩሲያ ጦርነትና እሱን ተከትሎ በታየው የዋጋ ንረት ምክንያት መስተጓጎል እንዳልገጠመው የቼክ ተቀዳሚ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጂሪ ኮዛክ አስታውሰዋል፡፡
ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና፣ በውሃ ልማት፣ በወጣቶች አቅም ማጎልበትና በጂኦሎጂካል ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እንደምትፈልግም ተናግረዋል፡፡
ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ባለፈው ዓመት ሀገሪቱ ባዘጋጀችው አዲስ የአፍሪካ ፕሮግራም ዋና ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን መግለፃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡