Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ነጋዴዎችና ዩኒየኖች ለመዲናዋ ነዎሪዎች የግብርና ምርቶችን ማቅረብ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ነጋዴዎችና ዩኒየኖች ለአዲስ አበባ ከተማ ነዎሪዎች የግብርና ምርቶችን ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ከመጋቢት 7 ቀን ጀምሮ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኦሮሚያ ነጋዴዎችና ዩኒየኖች የግብርና ምርቶች ለገበያ ትስስር ቀርቧል።

በገበያው ላይ ጤፍ ፣ ስንዴ ፣ በቆሎ ፣ ገብስ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶችም ቀርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ከዛሬ ጀምሮ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በብዛት በ10 አካባቢዎች ምርት የማቅረብ ስራ ይሰራል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ገልጸዋል።

የአቅርቦት ስራው የገበያ ትስስርም በመፍጠር እጥረቱና የዋጋ ውድነቱ እስኪቀረፍ ድረስ ይቀጥላልም ብለዋል።

ምርት በበቂ ሁኔታ አለ ያሉት አቶ አወሉ፥ ያጋጠመው እጥረትና የዋጋ ውድነት ሆን ተብሎ በአንዳንድ ነጋዴዎች የተፈጠረ እንደሆነም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቢኒያም ምክሩ ፥ በከተማዋ በተፈጠረ የምርት እጥረት የጤፍ ዋጋ መወደዱን በማንሳት ችግሩን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር ምርት ማቅረቡን ገልጸዋል።

ዛሬ በሳርቤት አደባባይ የተጀመረው ምርት የማቅረብ ስራ በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎችና የሸማች ማህበራት እንደሚቀጥልም አቶ ቢኒያም ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ምርት የሚደብቁ እና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይም ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግና እርምጃም እንደሚወስድ አሳስበዋል።

በቀረበው ምርት አንድ ኪሎ ጤፍ በ50 እና 56 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.