አሜሪካ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ተግባራዊነትን ተከትሎ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኗን አንቶኑ ብሊንከን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ ተግባራዊነት ተከትሎ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ እድል ተጠቃሚነት ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኗን በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ፡፡
አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ቆይታቸው በተለይም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቃለመጠይቁም ዩናይትድ ስቴትስ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኑን ነው የገለፁት።
ይህም አሜሪካ፥ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ በሚመለከታቸው አካላት ሙሉ በሙሉና ዘላቂነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ሲደረግም አሜሪካ ኢትዮጵያን ምርቶቿን ከኮታና ቀረጥ ነፃ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንድታስገባ ወደ ሚፈቅደው የአጎዋ ተጠቃሚነት ዳግም ለመመለስ ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር የጀመረችውን ጥረት ያደነቁት አንቶኒ ብሊንከን፥ የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ሒደት በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሰላም ስምምነት መደረሱ እና የትግበራ ሒደቱ በግጭት የተጎዱ ዜጎችን ህይወት እንደሚያሻሽል ጠቁመው፥ የኢትዮጵያ መንግስትም ስምምነቱን ለመተግብር እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ችግር ወደ ትግራይ ክልል እየገባ መሆኑን እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ዳግም ስራ መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡
የጦር መሳሪያ ድምጽ መቆሙን፤ ህወሓት ትጥቅ መፍታቱን እና ከትግራይ ክልል ሌሎች ሃይሎች እየወጡ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ የሰላም ስምምነቱ የእስካሁኑ አፈፃፀም ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ እንድትመለስ የሚያስችል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
በዮናታን ዮሴፍ