Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት እየፈፀመ ያለበትን ቁርጠኝነት አደነቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት ለሰሜኑ ግጭት በዘላቂነት ሰላማዊ አልባት ለመስጠት በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ የተደረሱትን ስምምነቶች እየፈፀመ ያለበትን ቁርጠኝነት አደነቁ።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት ወቅት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
 
በዚሁ ቃለ መጠይቅ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትከህወሓት ጋር በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ የተፈራረማቸውን ስምምነቶች በቁርጠኝነት ለመፈፀም እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
 
የሰላም ስምምነቱ እና አፈፃፀሙ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በማንሳትም፥ የሰው ህይወትን ለመታደግም ሆነ በጦርነቱ የተጎዱትን ሰዎች ህይወት ለመለወጥ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
 
ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በነበሯቸው ውይይቶች ወቅትም የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኝነት መኖሩን እንደተመለከቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
 
አክለውም በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የባንክ እና የዓየር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር የሚያበረታታ እርምጃ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
 
እነዚህ እርምጃዎች በጦርነት ውስጥ የነበሩትን አካባቢዎች እና ነዋሪዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የሚያስችሉ ናቸው ብላ አሜሪካ እውቅና እንደምትሰጥ ብሊንከን ገልፀዋል።
 
ሲያጠቃልሉም ሁሉም የሚመለከተው ወገን ለሀገሪቱ እና ለህዝቦቿ ጥቅም ሲል ስምምነቱን ያለምንም ችግር ተፈፃሚ እንዲሆን የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ነው በትኩረት የተናገሩት።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የስራ ሃላፊዎችን አግኝተው ተወያይተዋል።
 
በዮናታን ዮሴፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.