አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤትና በቡድን 20 አባል ሀገራት ቋሚ ውክልና እንዲኖራት የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ ትደግፋለች – አንቶኒ ብሊንከን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት እና በቡድን 20 ሀገራት ስብስብ ውስጥ ቋሚ ውክልና እንዲኖራት የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ፡፡
አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ቆይታቸው በተለይም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም ዩናይትድ ስቴትስ÷አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና ቡድን 20ን በመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ተቋማት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አፍሪካ ይህን ውክልና እንድታገኝ አሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ እንደምትሰጥ ነው ያረጋገጡት፡፡
አንቶኒ ቢሊንከን÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሚፈጠሩ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ከማድረግ አንጻር ቀዳሚ ሚና እየተወጣች መሆኑን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ በመጀመሪያ የሚጠቅመው ሀገሪቱን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ቀንድ ብሎም የመላው አፍሪካ ማዕከል መሆኗን ያሳያል ብለዋል፡፡
በዚህ ምክንያትም አሜሪካ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አፍሪካ የቀዳሚነት ሚናዋን በሚገባ እንድትወጣ ትፈልጋለች ነው ያሉት ፡፡
የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን ከመፍታት ረገድ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር ሆኖ መቀጠሉንም አስረድተዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከአፍሪካ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በዮናታን ዮሴፍ