Fana: At a Speed of Life!

ግብፅ ኃላፊነት ከጎደለው ንግግር እና ማስፈራሪዎቿ እንድትታቀብ ኢትዮጵያ አሳሰበች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የህዳሴ ግድብን በተመለከተ “ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” በማለት የሰጡትን መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ሲል ውድቅ አደረገ።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ፥ ግብጽ የዓባይ ግድብን አስመልክታ ለኢትዮጵያ ማስፈራሪያ የታከለበት መግለጫ ሰጥታለች ብሏል፡፡

ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር እና የአፍሪካ ህብረት ድንጋጌን በግልጽ የሚጥስ መሆኑን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ይህ ድርጊት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ራሷኑ ግብጽና ሱዳን በፈረንጆቹ መጋቢት 2015 ያደረጉትን ስምምነት የጣሰም ነው ብሏልሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡

በዚህም ግብጽ ተገቢ ያልሆኑና ህገወጥ መግለጫዎችን ከማውጣት እንድትቆጠብ አሳስቧል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የሚመለከታቸው አካላት ግብጽ የዓለም አቀፉ ግንኙነት ደንብን እየጣሰች መሆኗን ልብ ሊሉ ይገባልም ነው ያለው።

ግብፅ በማስፈራራትና ከህግ ውጭ ነገሮችን በማድረግ ፍላጎቷን ልታሳካ እንደማትችልም ሚኒስቴሩ አረጋግጧል፡፡

ሆኖም በመከባበርና በመተማመን እንዲሁም የዓለም አቀፉን ህግ ባከበረ መልኩ ከሆነ ሀገራቱ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መግባባት ላይ ይደረሳሉ የሚል ጽኑ እምነት እንዳለውም ነው የገለጸው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያ አሁንም ሁሉም ወገን አሸናፊ እንዲሆን የሚል አቋማ ላይ እንደሆነችም አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.