በድርቅና በግጭት ሳቢያ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈያ ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት ተቋም (ኤፍ አይ ዲ ኦ) በድርቅ እና በግጭት ምክንያት የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡
ተቋሙ ለአንድ ዓመት በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ በድርቅ፣ በምግብ እጥረት፣ በግልና አካባቢ ንፅህና ችግሮች እና በግጭቶች ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና እና የሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት ሲያቀርብ መቆየቱ ተጠቁማል፡፡
በዚህም ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
የተቋሙ የአንድ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ እና አዲስ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ÷ ፈያ ኢንትግሬትድ ዴቨሎፕሜንት ተቋም እና መሰል ሀገር በቀል ተቋማት ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን የጤና ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የጤና ሚኒስቴር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ በሶስቱ ክልሎች በድርቅ እና በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የተቀናጀ ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የአመጋገብ፣ ንፅህና አጠባበቅ እና የድንገተኛ አደጋ ግብረ መልስ ድጋፍ የሚያደርግበትን አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
በዚህ በሁለተኛው አዲስ ፕሮጀክትም ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ማቀዱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡