የተጭበረበረ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሰጡ ተከሳሾች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 500 ካሬ ሜትር ቦታ የተጭበረበረ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሰጡ 8 ተከሳሾች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጡ፡፡
ተከሳሾቹ የቀድሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ ሁለት የወረዳው የመሬት ልማት ባለሙያዎችና አምስት ግለሰቦች ናቸው።
ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር በአካባቢው አርሶ አደር ያልሆነ ግለሰብን አርሶ አደር ነው በማለት በቦታው ላይ ቤት ሰርቶ ለማይኖር ግለሰብ በወቅቱ የሊዝ ጨረታ ዋጋ 1ሚሊየን 63 ሺህ 835 የሆነ 500 ካሬ ሜትር ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በማዘጋጀት እንዲሰጥ አድርገዋል።
በዚህም አቃቤ ህግ ግለሰቦቹን በዋና ወንጀል አድራጊነት እና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስረቶባቸዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ ችሎት ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ፍርድ ቤቱ 3ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ያቀረቡት የቅጣት ማቅለያዎች አብዛኞቹ ተቀባይነት አግኝቷል።
በዚህም 3ኛ ተከሳሽ በ2 አመት ከ9 ወር እና በ1ሺህ ብር የገነዘብ መቀጮ ሲቀጣ፤ 6ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ3 አመት ከ7 ወር እና በ2 ሺህ ብር የገነዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 6 ተከሻሾች ደግሞ እያንዳንዳቸውን በ6 አመት ጽኑ እስራት እና በ11 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
በአልማዝ መኮንን