Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የኃይል መቆራረጥ በውሃ ምርት እና ስርጭት ላይ ችግር እንደፈጠረበት ባለስልጠኑ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ለደንበኞቼ የሚገባቸውን አገልግሎት በአግባቡ እንዳልሰጥ አድርጎኛል አለ፡፡

ከመጋቢት 1 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ቀናት በባለሥልጣኑ የውሃ ጉድጓዶች እና የግፊት ጣቢያዎች ላይ በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ማጋጠሙን በባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሠርካለም ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

ይህም በባለስልጣኑ የውሃ ምርት እና ስርጭት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ነው ዳይሬክተሯ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡

በኃይል መቆራረጡ ምክንያት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ 2፣3፣ 5፣ 12፣ 13 እና 14፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣2፣3፣4፣5፣6 እና 10 እንዲሁም በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2፣3፣4፣5፣6፣9፣10፣11፣12፣13 እና 14 የውሃ አቅርቦቱ ተቋርጧል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣9 እና 10፤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 13፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 6 እና ከወረዳ 9 እስከ 11 የውሃ አቅርቦቱ መቋረጡን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 1 እስከ 15፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ 2፣ 11 እና 12፤ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እና 5 በከፊል እና ወረዳ 9 በሙሉ እንዲሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የውሃ አገልግሎቱ መቋረጡን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የውኃና ኢትዮ ቴሌኮም ኤሌክትሪፊኬሽን፣ ኦፕሬሽን እና ሜንቴናንስ ቢሮ ኃላፊ ሱራፌል ሰይፈ በበኩላቸው÷ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ በመኖሩ በተለያዩ ቦታዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ አጋጥሞ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ክፍሉ ለውኃ እና ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ÷ ከአራቱም ዲስትሪክቶች ጋር በመተባበር የኤሌክትሪክ መስመሮችን በተቻለ ፍጥነት ወደ አገልግሎት ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት።

በውኃ ጉድጓዶቹ አካባቢ አማራጭ ኃይል ባለመኖሩ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሲያጋጥም የውሃ አገልግሎት ሊቋረጥ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በዋና ዋና የውኃ ጣቢያዎች የኃይል አገልግሎት ሲቋረጥ በአማካይ እስከ 30 ደቂቃ ባለው ጊዜ በድጋሚ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.