Fana: At a Speed of Life!

ከብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ታላቅ ምእራፍ በምትሻገርበት ድልድይ ላይ ትገኛለች፡፡ አንዳንዶች ከድልድዩ ወደኋላ ሊመልሷት ይታገላሉ፡፡ ሌሎቹ ድልድዩን ሰብረው ገደል ሊከቷት ይለፋሉ፡፡ ታጋይ ልጆቿ ደግሞ በድልድዩ ላይ ብዙ ሳትቆይ ወደፊት እንድትራመድ ለማድረግ ይታገላሉ፡፡ ብልጽግና ሦስተኛውን መርጧል፡፡
 
ድልድይ ያለፈውን መንገድ ያህል ጠንካራ አይሆንም፡፡ ገደሉን ለመሻገር ግን የግድ ነው፡፡ ረዥም ጊዜ በድልድዩ ላይ መቆየትም አደጋ አለው፡፡ በቶሎ መሻገርና ወደጸናው መሬት መድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለንበት የሽግግር ጊዜም የሚነግረን ይሄንን ነው፡፡ የሽግግሩ ወቅት ዓላማው በዚያው መቆየት ሳይሆን ወደ በለጸገች ኢትዮጵያ መሸጋገሪያ ነው፡፡ እየገጠሙን ያሉትም የሽግግር ጊዜ ፈተናዎች ናቸው፡፡
 
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 7- 8 ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ ካለፈው መንገድ የመጣችበትን፣ ወደ ብልጽግና ለመሻገር በድልድዩ ላይ የቆየችበትን፣ በድልድዩ ላይ በቆየችባቸው ወቅቶች የገጠሟትን ፈተናዎች፤ ከድልድዩ ወደኋላ ለመመለስ የሚታገሏትን ኃይሎች፣ ድልድዩን ተሻግራ ወደ ብልጽግና እንዳትሸጋገር ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በዝርዝር መርምሯል፡፡
 
አሁን እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች በዋናነት ከአምስት ነገሮች የመጡ መሆናቸውን የፓርቲያችን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አምኗል፡፡ ለእነዚህም ተገቢ ነው ያለውን የትግል ስልት ቀይሷል፡፡
 
መላ ኢትዮጵያውያንም እነዚህን ፈተናዎች ለማሸነፍ እንዲቻል ከብልጽግና ጋር አብረው እንዲታገሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የመጀመሪያው ፈተና ታሪክ ካሸከመን ዕዳዎች የሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አያሌ አኩሪ ታሪኮችና በታሪክ ውስጥ ያገኘናቸው ዕድሎች አሉን፡፡ በእነዚህ እንኮራለን፤ ለኢትዮጵያ ብልጽግናም እንደ አንጡራ ሀብት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸውና ያልተግባባንባቸው ዕዳዎችም አሉን፡፡ እነዚህ ዕዳዎቻችን የእኛ ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም ላይ ሀገር የመሠረቱ ሕዝቦች ሁሉ የሚገጥሟቸው ናቸው፡፡
 
እነዚህ ዕዳዎች የመነታረኪያ፣ የመጋጫና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑብን አይገባም፡፡ ዕዳዎቹን ወረስናቸው እንጂ አልፈጠርናቸውም፡፡ መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም፡፡
 
የተሻለው የመጀመሪያ መፍትሔ ለዕድሉም ለዕዳውም ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዕድሉን ለመጠቀም፣ ዕዳውን ደግሞ ለማራገፍ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠነና የሰከነ አካኼድ አዋጪ መሆኑን የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡
 
ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በጠብ፣ በግጭትና በመከፋፈል ለመፍታት የሄዱ ሀገሮች ተጨማሪ ዕዳ አመጡ እንጂ መፍትሔ አላገኙም፡፡ ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በሠለጠነና በሰከነ መንገድ በምክክርና በውይይት፣ በይቅርታና በዕርቅ ለመፍታት የሞከሩ ሀገሮች ግን ወደተሻለ መግባባትና ወደላቀ አንድነት ለመምጣት ችለዋል፡፡ እኛም የሚያዋጣን ይሄ ነው፡፡ የጀመርነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ እናድርግ፡፡
 
ለስኬቱም ከሁላችን የሚጠበቀውን ድርሻ እንወጣ፡፡ ዕዳዎቻችንን በምክክር፣ በይቅርታና በዕርቅ እናርማቸው፡፡ ያለፉ ነገሮቻችን ትምህርት እንጂ እሥር ቤት እንዳይሆኑን አድርገን እንሻገራቸው፡፡
 
የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ሕዝባችን ያለፉ ታሪካዊ ዕዳዎቻችንን እንደ ግጭት መሣሪያ ለመጠቀም የሚሹ ኃይሎችን በመታገል፣ ለሀገራዊ ምክክሩ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
 
ሁለተኛው ፈተና ነጻነትን ለማስተዳደር አለመቻል ነው፡፡ ነጻነት በነጻ አይገኝም፡፡ በነጻም አይቀጥልም፡፡ ለማግኘት መሥዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ በነጻነት ለመኖር ደግሞ ኃላፊነትን መሸከም ያስፈልጋል፡፡ ከመሥዋዕትነትና ከኃላፊነት ውጭ ነጻነት አይኖርም፡፡ ሕዝባችን ባደረገው መራራ ትግል ካገኛቸው መብቶች አንዱ ነጻነት ነው፡፡ አካባቢን የማስተዳደር፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጥ፣ መንግሥትን የመቃወም፣ ሚዲያን የማቋቋምና የመጠቀም፣ እምነትን ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት የማምለክ፣ ወዘተ. ነጻነቶችን ሕዝባችን በትግሉ ተጎናጽፏል፡፡
 
እነዚህ ነጻነቶች ግን በራሳቸው አይቆሙም፡፡ የማድረግ መብት ባለበት ሁሉ ያለማድረግ ኃላፊነት አለ፡፡ ያለ ማድረግ መብት ባለበት ሁሉም የማድረግ ኃላፊነት አለ፡፡ የሞራል፣ የባህል፣ የሕግ ተጠያቂነቶች ነጻነትን በኃላፊነት እንድንጠቀምበት የሚያስገድዱን ናቸው፡፡ ነጻነት የሌለበት የኃላፊነት ሥርዓት ጭቆናን ያስከትላል፡፡ ኃላፊነት የሌለበት የነጻነት ሥርዓትም ሥርዓት አልበኛነትን ያመጣል፡፡
 
 
በአካባቢ አስተዳደሮች፣ በሚዲያዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአክቲቪስቶች አካባቢ የሚስተዋለው ነጻነትን የማስተዳደር ችግር፣ በቶሎ ሊገራ የሚገባው መሆኑን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ በነጻነት መተዳደር ማለት ሕግ በማክበር፣ ሌሎችን ሳይጎዱ፣ ሀገር ሳያፈርሱና ግጭት ሳይቀሰቅሱ፣ መብትን ለመጠቀም መቻል ነው፡፡ ሕግ እያፈረሱ፣ የሌሎችን መብት እየጣሱ፣ ግጭትና ጥላቻን እየቀሰቀሱ፣ ብሎም ሀገር እያተራመሱ መንቀሳቀስ ግን ወንጀል እንጂ ነጻነት ሊሆን አይችልም፡፡ ወንጀል ደግሞ የሕግ ተጠያቂነትን ማስከተሉ የግድ ነው፡፡
 
በመሆኑም በሀገራችን ነጻነትን ማስተዳደር ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ምልክቶች እያሳዩ ነው፡፡ በነጻነት ስም በሚፈጸም ወንጀል የተነሣ በትግላችን ያገኘነውን ነጻነት እያጣነው ነው፡፡ ነጻነት ከኃላፊነት ጋር ሚዛናዊነቱን ጠብቆ እንዲሄድ የመንግሥት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች፣ የፍትሕ ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባችሁን እንድታደርጉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡
 
 
ሦስተኛው ፈተና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየገነገኑ መምጣታቸው ነው፡፡ ዛሬ ባለችው ኢትዮጵያ ማንም የበላይና የበታች ሆኖ መኖር አይችልም፡፡ አንዳችን ያለ ሌላችን ልንኖር አንችልም፡፡ በመከፋፈልና በመለያየት፣ በግጭትና በጥላቻ ምንም ዓይነት ዕድገትና ብልጽግና አይመዘገብም፡፡ ሰላምና ደኅንነታችንም አይረጋገጥም፡፡
 
እንደ ውሻ አጥንት ከጠላት በሚወረወርልን አጀንዳ እየተራኮትን፣ ለልማት የምናውለውን ጉልበትና ጊዜ ለሤራ ትንተና እያባከንን፣ አንድ ጋት ወደ ብልጽግና ፈቀቅ ልንል አንችልም፡፡ ሀገር መውደድ ሌላውን ወገን በመውደድ እንጂ በመጥላት አይገለጽም፡፡ ለሌላው ወገን መሥዋዕትነት በመክፈል እንጂ በግጭትና በትንኮሳ አይለካም፡፡
 
የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮችና ድርጊቶች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊዎች ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ የፓርቲና የመንግሥት አመራሮች ችግሮች በውይይት እና በሕግ አግባብ ብቻ እንዲፈቱ ማድረግ አለባቸው፡፡
 
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና መሠረት እንዲይዙ መሥራት አለባቸው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲጠናከር፣ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ መታገል በዋናነት ከአመራር የሚጠበቅ ሚና መሆኑን ለአፍታም ልንዘነጋው አይገባም፡፡
 
የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲጠበቁ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡ የሚመለከታቸው የፍትሕና የጸጥታ አካላትም ይሄን መሰል ንግግሮችንና ተግባራትን በቸልታ እንዳይመለከቱ ያሳስባል፡፡
 
አራተኛው ፈተና የኑሮ ውድነት ነው፡፡ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ባጋጠሙ ችግሮች የተነሣ በተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ መምጣቱን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ከኑሮ ውድነቱ ጋርም የሥራ አጥ መጠኑ ጨምሯል፡፡ ችግሩን በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ለመፍታት ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡ ፈተናውን በብቃት ለመሻገር መንግሥት መራር ውሳኔ ሊወስንባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም አረጋግጧል፡፡
 
 
ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ ጊዜያዊ ርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ በተለይም በችግሩ ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ አካሄዶችን ማረም የሚገባ ነው፡፡ ምርትን በተገቢ መጠን ለማምረትና ወደ ገበያ ለማድረስ የሚታዩ የአመራርና የአሠራር ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡ በየአካባቢው የሚዘረጉ ኬላዎች ከሕግ አግባብ ውጭ የሚያካሂዱት እገዳና ዘረፋ በአመራር ቁርጠኝነትና ሕግን በማስከበር ሊፈታ ይገባዋል፡፡
 
የሕዝቡን ችግር በማባባስ ኪሳቸውን መሙላት በሚፈልጉ ስግብግቦች ላይ አስተማሪ ርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ያለው ሠንሠለት እንዲራዘም በሚያደርጉ ደላሎችና ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ይገባዋል፡፡ ኢንቨስትመንትን፣ ንግድንና የሥራ ፈጠራን የሚያቀላጥፍ አሠራር መዘርጋት አለብን፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲደናቀፍ በሚያደርጉ አመለካከቶች፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ተገቢውን የእርምት ሥራ መሥራት ይገባናል፡፡
 
ለዚህም መላው የፓርቲያችን አመራርና አባላት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት የሚጠበቅባቸውን በቁርጠኝነት እንዲወጡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡ የሥራ አጥነትን ለመቀነስ የተጀመሩ ተነሣሽነቶች በተፋጠነና ትርጉም በሚያመጣ መንገድ እንዲከናወኑ፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ ለተሠማሩ አካላትም አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
አምስተኛው ፈተና ሌብነት ነው፡፡ አራት ኃይሎች የጋራ ግንባር ፈጥረው እየፈጸሙት ያሉት ሌብነት የድህነት ወገባችንን እያደቀቀው መሆኑን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአጽንዖት ተመልክቶታል፡፡ በመንግሥት ውስጥ የሚገኙ ሌቦች፣ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉ ሌቦች፣ በብሔር ዙሪያ ያሉ ሌቦችና በሚዲያው አካባቢ ያሉ ሌቦች ለአንድ ዓላማ አራት ሆነው እየሠሩ ሀገር እያጠፉ ነው፡፡
 
በመንግሥት አካባቢ የሚገኙት ሌቦች መዋቅርና ሥልጣናቸውን ይጠቀማሉ፤ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉት ሌቦች ደግሞ ገንዘባቸውን ለበለጠ ስርቆት ይጠቀማሉ፤ በብሔር ዙሪያ ያሉት ደግሞ ለሌብነታቸው የብሔር ሽፋን ይሰጡታል፡፡ በሚዲያ አካባቢ ያሉት ደግሞ የሌቦቹን ገጽታ ይገነባሉ፤ ሌቦቹ ሲያዙም ብሔራቸውን እየጠቀሱ ሕዝብ የተነካ ያስመስላሉ፡፡ ሁሉም ዓይነት ሌቦች ፍትሐዊነትን ያዛባሉ፤ የሕዝብን ደም ይመጣሉ፤ ስርቆታቸው እንዳይደረስበት ግጭትና ዐመጽ ያቀሰቅሳሉ፡፡
 
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ሌቦች ለማጥፋት የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እጃቸውን አስቀድመው ንጹሕ በማድረግ ትግሉን እንዲመሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡ ሕዝባችንም በሌቦች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ግቡን እንዲመታ መረጃ በመስጠት፣ የሌቦች ተባባሪ ባለመሆንና ከሌብነት የጸዳ ትውልድ በማነጽ ኢትዮጵያን እንዲታደግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
 
በአጠቃላይ ሀገራችን በወሳኝ ምእራፍ ላይ መሆኗን የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገምግሟል፡፡ ከሁለት ዓመቱ የጦርነት ጫና እየተላቀቅን ነው፡፡ በየአካባቢው የሚገኙ ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የሠራነው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡ በግብርና ምርት የተሻለ ውጤት እያገኘን ነው፡፡
 
በሥራ ዕድል ፈጠራ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ የነበሩብንን ፈተናዎች እየተሻገርናቸው እንገኛለን፡፡ የምናገኘው ርዳታና ብድር እየጨመረ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሦስት ዋና ዋና ኢኮኖሚዎች አንዱ ሆኗል፡፡ በገበታ ለሀገር የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ ናቸው፡፡
 
እነዚህን ተስፋ ሰጪ ጅምሮቻችንን ለማጨናገፍ ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ፈተናዎችን መሻገር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እንደ ብረት ማጠንከር ወሳኝ ነው፡፡ ተግባራችንና ንግግራችን የታረመና ሕዝብን ወደ ብልጽግና የሚወስድ መሆኑን በየጊዜው ማረጋገጥ አለብን፡፡ ትኩረታችንን በልማት፣ በሰላምና በደኅንነታችን ላይ ብቻ እናድርግ፡፡
 
ነጻነታችንን በኃላፊነት ማስተዳደር የግድ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ፣ ልማታችንንም የሚያፋጥኑ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ርምጃዎችን መውሰድ ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን ነው፡፡ ዲፕሎማሲያችንን ማስፋትና ማጽናት ቁልፍ ተግባራችን ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ በታሰበለት ጊዜ፣ ዕቅድና ሁኔታ እንዲካሄድና እንዲሳካ ማድረግ ኢትዮጵያ እንዲሳካላት ማድረግ ነው፡፡
 
የፕሬስ ነጻነትን በተገቢው ሕግ፣ ልክና መጠን፤ ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅም ቅኝት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይገባል፡፡ የእምነት ተቋማት የሕዝብን ሞራልና ዕሤት በመገንባት፣ በሰላምና በልማት ላይ በመሠማራት፣ ለኢትዮጵያ ብልጽግና የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ተስፋ ይደረጋል፡፡
 
በመሆኑም የፓርቲያችን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን፡-አራቱን ተገዳዳሪ ፈተናዎቻችንን አሸንፈን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያላትን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የጀመርነው ጉዞ እንዲሳካ፣ ዕውቀታችሁን፣ ጉልበታችሁንና ገንዘባችሁን በመሠዋት የትግሉ አካል እንድትሆኑ፣ የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ ያቀርባል፡፡
 
መጋቢት 8 ቀን 2015
 
አዲስ አበባ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.