Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በ2014/2015 የምርት ዘመን ከ202 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2014/2015 የምርት ዘመን ከ202 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊ ሃይሉ አዱኛ የክልሉን አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ እና በገበያ ላይ የተፈጠረውን ምርት እጥረት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በ2014/2015 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ በክልሉ የተሻለ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ 202 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸው÷ የተሰበሰበው ምርት ካለፈው የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ7 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።

በተጨማሪም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን የተቻለ ሲሆን ÷ እስካሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።

የክልሉ ምርታማነት በመጨመሩ በቂ ምርት መኖሩን ጠቅሰው÷እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በአንዳንድ አካላት ዘንድ የኑሮ ውድነትን ለማባባስ ምርት የመደበቅና የማከማቸት አዝማሚያ መኖሩን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመፍታት በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ምርት እየቀረበ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከዚህም ባለፈ ምርት የሚደብቁና በህገ ወጥ ንግድ ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።

በተያያዘም በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና እስካሁን የተለያዩ አካላት በተሳተፉበት የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ መሰብሰቡን አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.