ከ177 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ177 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ፡፡
በተጨማሪም የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ ዘጠኝ ግለሰቦች እና 12 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ከመጋቢት 1 እስከ 7 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ክትትል 128 ነጥብ 5 ሚሊየን የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 48 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የወጭ በድምሩ 177 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሐኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሐዋሳ፣ ሞያሌ እና አዋሽ፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ÷ በቅደም ተከተላቸው 37 ሚሊየን፣ 28 ሚሊየን እና 24 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ እንደቻሉ ተጠቅሷል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በፍተሻ፣ በብርበራና በጥቆማ እንደተያዙም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡