በወጪ ንግድ ስርዓቱ ክፍተት ከሀገሪቱ የተለያዩ ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ ይወጣሉ- አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በወጪ ንግድ ስርዓቱ ላይ ባለው ክፍተት ከሀገሪቱ የተለያዩ ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ እንደሚወጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሀገራዊ የቅንጅት መድረክ በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ደመቀ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “የተለያዩ ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እየወጡ አንጡራ ሀብታችንን እያሳጡን ነው” ብለዋል፡፡
ባለፉት አመታት ከውጭ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ በተሰሩ ስራዎች ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ስራዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።
ስለሆነም ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ይበልጥ ለማነቃቃት ኢንቨስትመንቱን ማበረታታትና ህገ ወጥነትን መግታት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ ለዚህ ደግሞ ክልሎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሀገራዊ የቅንጅት መድረክ በ2003 ዓም በተደራጀ መልኩ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።
በዛሬው ጉባኤ የውጭ ኢንቨስትመንት ስርዓቱን ለማሳለጥ በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም የፀረ ኮንትሮባንድ ብሔራዊ ኮሚቴ ስራን መገምገም ላይ ትኩረት ይደረጋል።
በታሪኩ ለገሰና ሃይማኖት ወንድራድ