Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት ላይ ከ 33 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ 1 ሺህ 785 ካሬ ሜትር ይዞታዎችን የልማት ተነሺ አርሶ አርሶአደሮች ናቸው በሚል በሀሰተኛ ሰነድ ለ30 ግለሰቦች በመስጠትና ያለአግባብ በመውሰድ በመንግስት ላይ ከ33 ሚሊየን 13 ሺህ 72 ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 85 ግለሰቦች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በ85 ተከሳሶች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ተደራራቢ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል።

የልማት ተነሺ ላልሆኑ ግለሰቦች የልማት ተነሺ አርሶአደሮች ናቸው በሚል ከፍተኛ ዋጋ ሊያስወጡ በሚችሉ በቸርችል ጎዳና ፣በመገናኛና ካራኤሎ አካባቢ የሊዝ ግምታቸው 58 ሚሊየን 601 ሺህ 735 ብር ካሳ እንዲሰራ በማድረጋቸውና በሀሰተኛ ሰነድ 1 ሺህ 785 ካሬ ሜትር ይዞታዎችን በመስጠት በመንግስትና በህዝብ ሀብት ላይ 33 ሚሊየን 13 ሺህ 72 ብር ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ነው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም የተከሰሱት፡፡

ከተከሳሾች መካከል የየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅት አስተባባሪ ወይዘሮ ምህረት ደስታ ፣2ኛ ተከሳሽ የየካ ክፍለ ከተማ የመሬት መረጃ ባለሙያ ዮሐንስ ፋንታ፣ 3ኛ የየካ ክፍለ ከተማ የሰነዶች አጣሪ ባለሙያ ታፈሰ ጎርፉ፣ 4ኛ ተከሳሽ የየካ ክፍለ ከተማ የሰነድ አጣሪ ባለሙያ መገርሳ መርጋ እና የየካ ክፍለ ከተማ የመረጃ ባለሙያ እመቤት ጌታቸው ይገኙበታል።

ተከሳሾች አጠቃላይ 85 ግለሰቦች ሲሆኑ÷ 39ኙ የክፍለ ከተማው የመሬትና መሬት ነክ ባለሙያዎች ናቸው ተብሏል።

ቀሪዎቹ 30 ግለሰቦች ደግሞ ያለአግባብ የልማት ተነሺ ተብለው በተለያየ መጠን ይዞታዎችን ወስደዋል የተባሉ ናቸው፡፡

ከ85 ተከሳሾች ውስጥ 18 ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን ቀሪዎቹ ተከሳሾች ግን በቁጥጥር ስር አልዋሉም።

መዝገቡ በ1ኛ ተከሳሽ በሆኑት የየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅት የስራ ሂደት መሪ በወይዘሮ ምህረት ደስታ ስም የተከፈተ ሲሆን፥ አጠቃላይ የ85 ተከሳሾች የወንጀል ተሳትፎ ተጠቅሶ ክስ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ችሎቱ የ18 ተከሳሾችን ማንነታቸውን በመለየት መዝግቧል።

የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ እና ያልቀረቡ ተከሳሾችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለመጋቢት 27 ቀን 2015ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ወንጀሉ የተፈፀመው ከ2010 እስከ 2014 ዓ.ም መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.