Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ የ14 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ለግብርና መካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል የ14 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት በበይነ መረብ በተከናወነ ስነ-ስርአት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሬታ ሰዋሰው እና የደቡብ ኮሪያ የቴክኖሎጂ ልህቀት ኢኒስቲትዩት ዳይሬክተር ጄነራል ቺዩን ፓርክ ፈርመውታል፡፡

የድጋፉ ዓላማ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን እና በሃገር ውስጥ የሚመረቱትን ምርቶች ወደ ተገልጋዩ ከመድረሳቸው በፊት የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ስለመመረታቸው የሚያረጋግጥ ማዕከል በመገንባት በጥራት እና ብቃት ማነስ ምክንያት በተጠቃሚው ላይ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ ማስቀረት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም በጥራት እና ብቃት ማነስ ምክንያት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ እና ወደፊትም ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት በመቀነስና በማስቀረት የሀገርን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማፋጠን አስተዋጽኦ ማድረግ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡

በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የመካናይዜሽን ስልጠና ፍተሻና ምርምር ማእከል ማቋቋም፣ በክልሎች ደረጃ የኦፕሬሽን እና ጥገና ማእከል ማቋቋም፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ማከናወን፣ የማስተዋወቅ እና የሰርቶ ማሳያ ተግባራን ማከናወን ፣ የማእከሉን ኦፕሬሽን ሞዴል ማዘጋጀት እና ለፕሮጀክቱ እገዛ ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ድጋፍ መስጠት ናቸው ተብሏል፡፡

የኦፕሬሽንና የጥገና ማእከላቱ በአዲስ አበባ ቃሊቲ፣ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ፣ በአማራ ክልል ቡሬ ከተማ፣ በደቡብ ክልል አላባ ከተማ እንደሚቋቋሙ ታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.