Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ።

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በክልሉ ቆላማ ወረዳዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያሉት ሀላፊዋ ከ900 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የክልሉ መንግስት 100 ሚሊየን ብር መድቦ ድጋፍ ማድረጉን በመጥቀስም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ህብረተሰቡ የላቀ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮንሶ ዞን፣ ቡርጂ፣ አማሮ፣ አሌ፣ ደራሼ ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም ኡባ ደብረ ጸሀይ፣ ገረሴ እና አባላአባያ ወረዳዎች ላይም ድጋፍ መደረጉን ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባሻገር ሲራሮ ባደዋቾ፣አቶቴ ኡሎ እንዲሁም ማረቆ ወረዳዎች ላይ ድጋፍ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኮንሶ እና በደቡብ ኦሞ ዞን በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ላይ የፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እያደረጉ ስለመሆኑም ነው ያነሱት።

ከችግሩ ስፋት አንጻር እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ያወሱት ኃላፊዋ ተጨማሪ የምግብ እህል የማቅረብ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በተለመለከተ በኮንሶ ዞን 3 እንዲሁም በደቡብ ኦሞ ዞን 3 የመጠጥ ውሃ ቦቲዎችን ማቅረብ መቻሉን የተናገሩት ኃላፊዋ ድጋፉ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ የውሃ ቦቲዎችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከጤናም አንጻር በድርቁ ተጎጂ የሆኑ አካላትን ልየታ በማካሔድ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በትምህርት ቤቶች ደግሞ የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች 40 ሚሊየን ብር በመመደብ ለአርሶ አደሩ የማካካሻ ዘር የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.