የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ደመቀ መኮንን ሕገ ወጥ የሃብት ዝውውር ከፍተኛ የሐገር ደህንነት ስጋት መሆኑን ገለጹ

By Mikias Ayele

March 20, 2023

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰው ሀብት ጀምሮ በሁሉም ጸጋዎች ላይ የሚታየው ሕገ ወጥ ዝውውር ከፍተኛ የሐገር ደህንነት ስጋት ሆኗል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

አቶ ደመቀ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷”ሀገራችን  የሰው ሀብቷ፣ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ሀብት፣ የግብርና ውጤቶችና የእንስሳት ሀብት ባለቤት ናት” ብለዋል።

እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት መንገድ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደመቀ፥ ሀብቶችን በሚገባ ጥቅም ላይ ለማዋል የውስጥ እና የውጭ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ሕገ ወጥ ንግድ በተለይም የኮንትሮባንድ ንግድ የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች የውስጥ አቅምን በልኩ እንዳንጠቀም እያወኩ ያሉ ሳንካዎች ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የገለፁት አቶ ደመቀ ከሰው ሀብት ጀምሮ በሁሉም ሀብቶች ላይ የሚታየው ሕገ ወጥ ዝውውር እና ንግድ በኢኮኖሚያዊ ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አስገንዝበዋል፡፡