Fana: At a Speed of Life!

ዕድሜያቸው ከ50 በላይ የሆኑ ሴቶች ለአጥንት መሳሳት ተጋላጭ ናቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለይም የወር አበባ ማየት ያቆሙ እና ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች በአጥንት መሳሳት አማካኝነት ለሚከሰት የአጥንት ህመም (ስብራት) ተጋላጭ እንደሆኑ ይገለጻል፡፡

ለአጥንት ህመም አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች አንዱ የአጥንት መሳሳት ብዙ ጊዜ ከሆርሞን ጋር ስለሚገናኝ ነው በሴቶች ላይ የሚስተዋለው፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ጤነኛ ሰው በተለይም ለአጥንት መሳሳት ተጋላጮች ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች የአጥንት ማጠንከሪያ ካልሽየም እና ቪታሚን ዲ እንዲወስዱ ይመከራል፡፡ ይህም በቀላሉ በአጥንት ላይ የሚያጋጥምን አደጋ ለመከላከል ያግዛል፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት÷ ከእጅ፣ እግር፣ አከርካሪ አጥንት፣ ዲስክ፣ መገጣጠሚያ እና ጅማት ላይ የሚነሱ ህመሞች፣ ዕጢዎች እንዲሁም በአደጋ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶች በአጥንት ሕክምና ይታያሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአጥንት ህመሞች በ14 ዓይነት ዘርፍ (ሰብስፔሻሊቲ) ሕክምናቸው ይሰጣል፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስታልም ስምንቱ (የከፍተኛ አደጋዎች፣ የሕጻናት፣ የአጥንት ካንሠር፣ የዳሌና የጉልበት መገጣጠሚያ፣ የእጅና ትክሻ፣ የእግርና ቁርጭምጭሚት፣ የጅማት፣ የጀርባ አከርካሪ አጥንትና የዲስክ ሕክምናዎች) በሰብ ስፔሻሊቲ ደረጃ ይሰጣሉ፡፡

ለአጥንት ህመም አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች መካከል÷ ዕድሜን ተከትሎ የሚመጣ የአጥንት መሳሳት፣ በተለያየ ሁኔታ የሚከሰቱ አደጋዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም የአጥንት ካንሠር እና የትራፊክ አደጋዎች ተጨማሪ አጋላጭ መንስኤዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ወንድምአገኝ ጥበቡ እንደገለጹት÷ የአጥንት ህመም እንደሚከሰትበት ቦታ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል፡፡

ከምልክቶቹ መካከል አደጋን ተከትሎ የህመም ስሜትና ቁስለት መኖር፣ መገጣጠሚያዎች ላይ እንዲሁም በትንሽ አደጋዎች የአጥንት መሰበር፣ በጀርባ አካባቢ የሚከሰት ህመም፣ መላ ሰውነትን የመቆረጣጠም (የመያዝ)፣ ጠዋት ከመኝታ ሲነሱ የእግር እና እጅ መገጣጠሚያዎችን የመያዝ ከእንቅስቀሴ በኋላ ለቀቅ የማድረግ ስሜት የሚሉት ይጠቀሳሉ ይላሉ፡፡

የትኛውም የአጥንት ህመም ሕክምና በሀገር ውስጥ እንደሚሰጥ አረጋግጠው÷ ምናልባት ከወረፋ ጋር በተያያዘ ሰዎች ላለመጠበቅ ሲሉ በራሳቸው ፈቃድ ከሀገር ውጭ እንደሚታከሙም ጠቁመዋል፡፡

የአጥንት ህመም በየትኛውም ጾታ እና ዕድሜ የመከሰት ዕድል እንዳለው ገልጸው÷ በተለይም አሁን ላይ የዕድሜ መጨመርን ተከትሎ የአጥንት ስብራት እየተበራከተ ነው ይላሉ፡፡

በተለይም ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች የወር አበባ ማየት ካቆሙ በኋላ አጥንታቸው ስለሚሳሳ ለአጥንት ህመም የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ÷ የአጥንት ማጠንከሪያ መድኃኒቶችን መውሰድ እና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም ከፍተኛ የካልሽየም ይዘት ያላቸውን ምግቦች፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ወተት በማዘውተር የአጥንት ጥንካሬን መጨመር ይቻላል ነው ያሉት፡፡

የአጥንት ህመም ስሜት ሲኖር በቶሎ ወደ ሕክምና በመሄድ መዳን ይቻላል ያሉት ባለሙያው÷ ጊዜ ከወሰደ ግን መዳን የማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል፡፡

ብዙ ጊዜ በባህል ለመታከም የሚደረጉ ጥረቶች ሕመሙን እንደሚያባብሱት ስጋታቸውን ገልጸው÷ በዚህ ሂደት ረጂም ጊዜ ስለሚወስዱ ወደ ጋንግሪን እና ካንሠር ተቀይሮ የአካል ክፍል እስከ መቆረጥ ደረጃ ይደርሳል ነው የሚሉት፡፡

ከአካል ክፍል መቆረጥ ባለፈም ለሞት ሊያደርስ እንደሚችል ነው ዶክተር ወንድምአገኝ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ያስገነዘቡት፡፡

ከባድ የዳሌ ገንቦ አጥንት ስብራት ከመጠን በላይ ደም መፍሰስ በማምጣት፣ አንገት አካባቢ ያለ አከርካሪ አጥንት የአተነፋፈስ ሥርዓትን በማዛባት ሕይወት ሊያሳጡ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.