በክልሎች በወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሔደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ፣ ሶማሌ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የከፍተኛ አመራሮች ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ እያካሄደ የሚገኘው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ አመራሮች ውይይት “ድሎችን የማጽናትና ፈተናዎችን የመሻገር ወቅታዊና ታሪካዊ የአመራር ተልዕኮ” በሚል ርዕስ ነው፡፡
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የከፍተኛ አመራሮች ውይይት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ÷ “እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ሀገር ለማፅናት የሚናበብ የዓላማ አንድነት ያለው አመራር ያስፈልጋል” ብለዋል።
ህዝቡ እያጋጠሙት ያሉ ችግሮችን በመፍታት አንድነቱን ማስጠበቅና ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድሎች በመቀየር ከህዝቡ የተቀበለውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም ጨምረው ጠቁመዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው ÷ከፍተኛ አመራሩ ለሀገር አንድነት በዓላማ የተደራጀ በሥነ-ልቦና አንድነት ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀውን የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሻሌ፣ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ አሪፍ መሀመድን ጨምሮ የክልል የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የውይይት መድረኩ አመራሩ በለውጡ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሚገባ ተገንዝቦ ለማስቀጠል ቁርጠኛ አቋም በመያዝ ፓርቲንና መንግሥትን በብቃት ለመምራት የሚያስችል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የሚያጎናፅፍ ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው።
ውይይቱም አመራሩ በለውጡ ዉስጥ የተገኙ ስኬቶችን ተገንዝቦ፣ እያጋጠሙ ያለዉን ዉስጣዊና ወጫዊ ተግዳሮቶች ተረድቶ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመፍጠር እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ ተናግረዋል።
እየተደረጉ ያሉት ውይይቶች ለሁለት ቀናት እንደሚቆዩ ከክልሎቹ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃ በጳውሎስ አየለ