Fana: At a Speed of Life!

በዳዋ ዞን ከ121 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን ከ121 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

በሶማሌ ክልል ባሉ 11 ዞኖች በተከሰተው ድርቅ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለተረጂነት ተጋልጠዋል።

በዋናነት በክልሉ በድርቁ ከተጎዱ ዞኖች መካከል የዳዋ ዞን አንዱ ሲሆን÷ በዞኑ ባሉ አራት ወረዳዎች ( በሙባረክ፣ ሞያሌ፣ ቀደዱማ እና በሁደት )ነው ድርቁ የተከሰተው።

በዚህም ምክንያት በዞኑ ከ121 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዳዋ ዞን ተወካይ አስተዳዳሪ አቶ አደን አሊ አደን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል።

በዞኑ ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ግመሎችን ጨምሮ ወደ 415 ሺህ የሚጠጉ እንስሳት የሞቱ ሲሆን÷ ወደ 1ሚሊየን የሚጠጉት ደግሞ እጅግ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች በተለያዩ መንግስታዊ እና አጋር አካላት ውስን ድጋፎች እየቀረቡ ያለ ቢሆንም ከድርቁ ስፋትና ሁሉም ነዋሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ድጋፉ በስፋት ተደራሽ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል።

እንዲሁም ከፌዴራል ፣ ከክልል እና ሌሎች እርዳታ ሰጪ ተቋማት ለተጎዱ ዜጎች የሚመጡ ድጋፎችን ከዞን ወደ ተለያዩ ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች በፍጥነት ለማድረስ የመንገድ ችግር ፈተና ሆኗል ነው የተባለው።

በዞኑ የተከሰተው ድርቅ በሰው እና በእንሰሳት ላይ ከዚህ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የሰብዓዊ እርዳታ በአፋጣኝ እንዲደርስም አቶ አደን አሊ አደን ጥሪ አቅርበዋል።

በመራኦል ከድር እና ሰዓዳ ጌታቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.