Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት “ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል” በሚል ያወጣችውን ሪፖርት እንደማትቀበል ኢትዮጵያ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት “በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል” በሚል ያወጣውን ሪፖርት እንደማይቀበል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ያደረጉት ምርመራ ውጤት ካስቀመጠው ግኝት አንፃር ሲታይም የአሜሪካ ሪፖርት አዲስ ነገር ያልጨመረ መሆኑን ነው ያመለከተው።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፥ ሪፖርቱ ሚዛኑን ያልጠበቀ፤ የአንድ ወገንን ብቻ መወንጀል ላይ ያነጣጠረ ባዶ ውንጀላ ስለመሆኑም ገልጿል።

መንግስት ተጠያቂነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮች ብሔራዊ ምክክርን ይፋ ባደረገበት ማግስት የወጣ ጊዜውን ያልጠበቀ ሪፖርት ስለመሆኑም ነው ያስታወቀው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መነሻው ምንም ይሁን ምን ሪፖርቱን ግን ሌሎች አንዱን ማህበረሰብ በሌላው ላይ ለማነሳሳት እና ጠባሳ ለመፍጠር ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንደሆነ ጠቁሟል።

በአጠቃላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሪፖርት ገለልተኝነት የጎደለው እና ከፋፋይ አካሄድን የተከተለ ነው ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዲሻሻል ተስፋን የሰጠ መሆኑን ጠቁሟል።

ይህ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ቢወጣም በአንቶኒ ብሊንከን ገብኝት ወቅት የተደረሱ መግባባቶች የሁለቱን ሀገራት ግኑኝነት እንደሚያሻሽሉ ተስፋ እንደሚያደርግ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮች ብሔራዊ ምክክርን ማጠናቀቅንን ጨምሮ ተጠያቂነትን ለማስፈን የኢትዮጵያ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች እንደሚቀጥል መግለጫው አረጋግጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.