Fana: At a Speed of Life!

የረመዷን ጾም ዛሬ ጨረቃ ከታየች ነገ ፣ ካልሆነ ግን ከነገ በስቲያ ይጀምራል – የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የረመዷን ጾም ማክሰኞ (ዛሬ) ጨረቃ ከታየች ረቡዕ (ነገ) ፣ ካልሆነ ግን ሐሙስ (ከነገ በስቲያ) እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት አስታወቀ።
 
ምክር ቤቱ የ1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የረመዷን ጾምን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
 
በመልዕክቱም÷ሙስሊሙ ሕብረተሰብ በጾም ወቅት የተለመደውን የእርስ በርስ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ተግባሩን በጾም ወቅት አጠናክሮ እንዲቀጥልበት ጠይቋል ።
 
የዘንድሮው የረመዷን ጾምን ስንጾም የተራቡትን የተቸገሩትን ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉትን በማስታወስ ሊሆን እንደሚገባም አንስቷል።
 
በረመዷን ወር ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከወትሮው በበለጠ ከፍ ባለ እርስ በእርሱና ከሌሎች ወገኖች ጋር የሚረዳዳበት ነው ብሏል ምክርቤቱ።
 
በተጨማሪም ይቅር የሚባባልበት የሚተዛዘንበት ወር በመሆኑ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከመቼውም ጊዜ በተለየ አቅመ ደካማ ወገኖቻችንን በመርዳት የተጣሉትን በማስታረቅና አብሮነታችንን በማጠናከር በመተባበር ሊሆን ይገባል ነው ያለው።
 
በዚህ በምንይዘው የረመዷን ጾም ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደወትሮው ሁሉ የሀገራዊ ሰላምና ልማት በሚያመጡ ጉዳዮች የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ምክርቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።
 
ፈጣሪ እንዲታረቀንና ምህረቱን እንዲያወርድልንም ቀኑን በጾም ለሊቱን ደግሞ በሰላትና በዱዓ በማሳለፍ የመጣብንን መከራ መሻገር የምንችለው ወደ ጌታችን ስንጠጋ ብቻ ነው ብሏል ።
 
በመሳፍንት እያዩ እና ቤተልሔም መኳንንት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.