ማኅበራዊ ዕሴትን አጽኝው – ረመዷን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኩርፊያን ከሚጸየፉ እና አብሮነትን ከሚተክሉ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ከሚከወኑበት ቁርዓን የወረደበት ወቅት እንደሆነ የሚነገርለት የረመዷን ወር አንዱ ነው፡፡
ጾሙ በኢትዮጵያ ከመካ ጋር እኩል እንደተጀመረም ይነገራል፡፡
የእስልምና ሐይማኖት ከተዋቀረባቸው አምስት ማዕዘናት አንዱ የረመዷን ጾም መሆኑንም የሐይማኖቱ ተከታዮች ይገልጻሉ፡፡
የረመዷን ጾም መግቢያ እና መውጫ በጨረቃ መታየት ላይ የተመሠረት ሲሆን÷ በየዓመቱ የሚመጣ እና ለ29 ወይም 30 ቀናት የሚጾም ነው፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ “ረመዷን ከምግብ ብቻ ሳይሆን ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ መቆጠብን ያስገድዳል” ይላሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ረመዷን በኩርፊያ አይጾምም፤ ሁሉም እንደአቅሙ ያዘጋጀውን እያቀረበ በጋራ የማፍጠር ሥነ ስርዓቱ ይከናወናል፤ ያለው ለሌለው ያካፍላል፤ ይተዛዘናል።
እንደ ሐይማኖቱ አስተምኅሮ ቂም ይዞ ረመዷንን መጾም ፍጹም ክልክል ስለሆነ ኩርፊያን እየተጸየፈ፣ አብሮነትን እየተከለ እና እያጸና ያለ የተቀደሰ ወር ተደርጎ እንደሚወሰድም ያስረዳሉ፡፡
ረመዷን ከሐይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ማኅበራዊ ትስስርን በማጥበቅ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ይህም አብሮ በመጸለይ፣ በመጠያያቅ፣ አንዱ ለሌላው ያለውን በማካፈል ብሎም በጋራ በመብላትና በመጠጣት እንደሚገለጽ ነው ያብራሩት፡፡
ነገ የሚብተው የረመዷን ጾም ዘንድሮ ለ1 ሺህ 444ኛ ጊዜ በእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ የጾም ሥነ ስርዓቱ ይከናወናል፡፡
ከረመዷን ጾም መግቢያ ቀደም ብሎ ያለው ጊዜ “ሻዕባን”ይባላል፡፡ ይህ ወቅት አማኞቹ ለረመዷን ጾም አልባሳትና ቁሳቁስን ንጹህ ማድረግን ጨምሮ እራሳቸውን ለተቀደሰው የረመዷን ወር በማዘጋጀት የሚጠብቁበት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የረመዷን ሌሊቶችን በመስጅዶች በሶላት እና ቁርዓን በመቅራት በዱዓ ማሳለፍ የተለመደ መሆኑን ጠቁመው÷ በናፍቆት እንደሚጠበቁም ነው የሚገልጹት፡፡
በሐማኖታዊ ትምህርት ቤቶችም ቁርዓን ከመቅራት ውጭ ያሉት መርሐ ግብሮች ረመዷን እስከሚጠናቀቅ ለጊዜው ይቆማሉ ነው የሚሉት፡፡
በረመዷን የሶላት መርሐ ግብር በንቃት እንደሚከናወን ጠቅሰው÷ በአንጻሩ የማይሰግድ እና የማይጾም ሰው ከእምነቱ እንዳጎደለ ይቆጠራል ብለዋል፡፡
በረመዷን ከመደበኛው አምስቱ ሶላቶች በተጨማሪ በእያንዳንዱ ቀን ተራዊህ ሶላት እንደሚሰገድም ነው ያመላከቱት፡፡
በጾሙ መጨረሻ ቀን በዓሉ በአደባባይ (በኅብረት) ይከበራል፡፡ ከመከበሩ ቀደም ብሎ በሌሊት ሁሉም በየቤቱ ደስብሎት እንዲያፈጥር የገንዘብ ችግር ላለባቸው ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
በረመዷን ወቅት የሚደረግ በጎ ተግባር ሁሉ በእጥፍ እንደሚከፈል የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር አደም÷ የተከበረች እና ፈጣሪ ላደረግነው ሁሉ ዋጋችንን የሚከፍልበት፣ የዱአችን ዋጋ የምናገኝበት እንዲሁም አላህ ምህረቱን የሚሰጥበት ጊዜ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
የጾምን ዋጋ የምሰጠው እኔነኝ ብሎ አላህ በነብዩ መሐመድ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም አማካኝነት መመሪያ መስጠቱን አስታውሰው÷ ጾም ለፈጣሪ ያለንን ክብር እና መታመን የምንገልጽበት ነው ብለዋል፡፡
የረመዷን የጾም ወቅት በ10 ቀናት ተመድበው በሦስት የሚከፈሉ ሲሆን፥ የመጀመሪያው 10 ቀናት የራኅማ (የእዝነት)፣ ሁለተኛው 10 ቀናት የምሕረት እና የመጨረሻው 9/10 ቀን ደግሞ ከእሳት መውጫ ቀን እንደሆነ ይታመናል ነው ያሉት፡፡
በሐይማኖቱ ተታዮች ዘንድ በሦስተኛው ሣምንት ካሉት9/10 ዕለታት አንዷ በልዩ ሁኔታ የተቀደሰች እንደሆነች አስረድተዋል፡፡
ዕለቷ የአማኙ ኃጢያት የሚሰረዝባት ስትሆን አንድ ሰው ያችን ዕለት በትጋት በጸሎት ካገኛት ከ1 ሺህ ዕለታት ጸሎትና ስግደት የበለጠ ዋጋ ያገኝባታል ብለዋል፡፡
የረመዷን ወር አላህን ይቅርታ በመጠየቅ ምንዳና በረከት የምናገኝበት እንዲሆን ህዝበ ሙስሊሙ ከወዲሁ ጾሎት በማድረግ ራሱ ከማዘጋጀት ባለፈ የእሱን እገዛና ድጋፍ የሚሹ ወገኞችንም በሚችለው ሁሉ በመርዳት ሊያሳልፍ እንደሚገባም አንስተዋል።
1 ሺህ 444ኛው ረመዷን ጾምን ህዝበ ሙስሊሙ ሲቀበል እስልምና የሚያዘውን ይቅርባይነትን በማብዛት፣ ከሃጢያት መራቅን እና እዝነት በማብዛት ለራሱና ለወገኞቹ የሚበጀውን መልካም መንገድ በመከተል ሊሆን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!