በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የመደመር ትውልድ መጽሃፍ የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ላይ ከ609 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት ምሽት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በተደረገ የመደመር ትውልድ መጽሃፍ የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ላይ ከ609 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል፡፡
የመደመር ትውልድ መጽሃፍ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የማስተዋወቅ እና ገቢ የማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የተካሄደው በገቢው የሶፍ ዑመር ዋሻ ልማት እና የቱሪስት መዳረሻ ቦታውን ምቹ ለማድረግ በማለም ነው።
በማስተዋወቂያ መርሐ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ባለሃብቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
ስነ-ስርዓቱ በአባ ገዳዎች ምርቃት ተጀምሮ ፥ የመጽሃፉን ይዘት በተመለከተ አጠር ያለ ዳሰሳ በመምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ዮሴፍ ቤኮ እና ዶ/ር ታደሰ ሌንጮ ተደርጓል።
መጽሃፉን የተለያዩ ባለሃብቶች እና ተቋማት በከፍተኛ ገንዘብ በመግዛት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፊርማ ያረፈበትን መጽሃፍ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እጅ ተቀብለዋል።
በዚህም በአጠቃላይ 609 ሚሊየን 220 ሺህ ብር ቃል መገባቱ ነው የተገለጸው፡፡
በስነ-ስርዓቱ መዝጊያ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፥ ˝ይህ መጽሃፍ የጠራ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ በመገንባት ኢትየጵያን ወደ ብልፅግና መንገድ የሚመራና የያዘችውን መንገድ ለማስቀጠል የሚያግዝ ነው’’ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የወደፊት የሶፍ ዑመር ዋሻ አጠቃላይ ገፅታ ንድፍ በክልሉ የቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ለታዳሚው ቀርቧል።
በታሪኩ ወ/ሰንበት
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!