Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በመሬት አገልግሎት ዘርፍ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፍ የማሻሻያ ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች እና ሌብነትን መቅረፍ የሚያስችል የማሻሻያ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ÷በመዲናዋ የመሬት እና መሬት ነክ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ብልሹ አሰራር እና ሌብነትን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ወራትም በስርቆት ተይዘው የታጠሩ መሬቶች እና ግንባታቸው ተጀምረው የቆሙ መሬቶችን ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሌሎች ተግዳሮቶችን መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን እና ሌብነትን ለመከላከል የሚያስችል ተቋማዊ የማሻሻያ ስራ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ህይወት ተፈራ÷በክፍለ ከተማው ለተገልጋዮች የቅሬታ ምንጭ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ከዚህ በፊት ሲሰራባቸው የቆዩ የመሬት ደንቦች እና መመሪያዎች ነባራዊ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻሉ እና ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

በመሬት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚከሰቱ ችግሮች ውስጥ 50 በመቶው ከመረጃ አያያዝ ጋር የተገናኘ ነው ያሉት ሃላፊዋ÷ችግሩን ለመፍታትም በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እየተቋቋመ ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ ለብልሹ አሰራር እና ሌብነት ምንጭ የሆኑ ባለሙያዎችን በመለየት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቢሮው ተገልጋዮችን ለአላስፈላጊ እንግልት የሚዳርጉ አመራሮች እና ሰራተኞች ሲያጋጥሙም ጥቆማ የሚሰጥበት አሰራር መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በክፍለ ከተማው በተለያዩ ብልሹ አሰራሮች የተጠረጠሩ 18 ሰራተኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለከተማ አስተዳደሩ ተላለልፈው መሰጠታቸውን ወ/ሮ ህይወት ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ አራዳ ፣ ቂርቆስ እና ሌሎች ክፍለ ከተሞች በመሬት እና መሬት ነክ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች እና ሌብነቶችን ለማስተካከል የሚያስችል የማሻሻያ ስራ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የሚያደረገው የማሻሻያ እና ስርዓት የማዘመን ስራ ስኬታማ እንዲሆንም ማህበረሰቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.