Fana: At a Speed of Life!

ቻድ ከ400 በላይ የሚሆኑ አማፂያን በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወሰነች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻድ ከ400 በላይ የሚሆኑ አማፂያን በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ መወሰኗን የሀገሪት ዐቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡

እስራቱ የተፈረደባቸው አማፂያን በፈረንጆቹ 2021 በቀድሞው የቻድ መሪ ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ግድያ ላይ የተሳተፉ ናቸው ተብሏል።

የዋና ከተማዋ ንጃሚና ዐቃቤ ህግ የሆኑት ማሃማት ኤል ሃጅ አባ ናና እንደገለፁት፥ አማፂያኑ በሽብርተኝነት፣ በቅጥረኝነት፣ ህፃናትን ለወታደርነት በመመልመል እና በሀገሪቱ መሪ ላይ ጥቃት በማድረስ ወንጀሎች የእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

በዚህም ከ400 በላይ የሚሆኑ አማፂያን በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን 24 አማፂያን ደግሞ ክሳቸው መቋረጡን አስረድተዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2021 መቀመጫውን ሊቢያ ያደረገውና ራሱን የለውጥ ግንባር እያለ የሚጠራው አማፂ ቡድን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጥቃት መክፈቱ ይታወሳል።

ጥቃቱን ተከትሎም ሀገሪቱን ለሶስት አስርት አመታት የመሩት ኢድሪስ ዴቢ መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡

ዴቢ ለስድስተኛ ጊዜ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን ምርጫ ካሸነፉ በኋላ በአማፂያኑ በደረሰባቸው ጥቃት ለህልፈት መዳረጋቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.