በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሶማሊያ ፍልሰተኞች 116 ሚሊየን ዶላር አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሶማሊያ ፍልሰተኞች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ 116 ሚሊየን ዶላር እንደሚስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ወር በሶማሊያ በተቀሰቀሰው ግጭት በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ያስታወሰው ኤጀንሲው÷ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ሶማሊያውያን ፍልሰተኞች ውስጥም አብዛኛዎቹ ሴቶች፣ ህፃናት እና አዛውንቶች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ስደተኞቹ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ የምስራቅ የአፍሪካ ዳይሬክተር ክሌመንት ንክዌታ ሳላሚ÷የኢትዮጵያ መንግስት እና የአካባቢው ማህበረሰብ ፍልሰተኞችን በመቀበል የሚችለውን እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለፍልሰተኞች እየጨመረ የመጣውን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን በአንጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አጋሮቹ ለፍልሰተኞች አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ 884 ሺህ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንደሚገኙም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡