Fana: At a Speed of Life!

ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ 168 ቦታዎች ተለይተው ተቋማት በትኩረት እንዲሠሩ ክፍፍል ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲ አበባ ከተማ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ 168 ቦታዎች ተለይተው በትኩረት እንዲሠራ ለባለድርሻ ተቋማት ክፍፍል መደረጉን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት÷ ጥገና የሚያስፈልጋቸው የተቆፋፈሩ መንገዶች እና በቆሻሻ የተደፈኑ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች መኖራቸውን ተመልክቷል።

ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ በወንዝ ዳር አካባቢ የተሠሩ የተለያዩ መጠለያዎች መኖራቸውንም ጣቢያችን ታዝቧል፡፡

ክረምቱ ሳይገባ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እንዲጠገኑና እንዲጸዱ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሰጥተዋል፡፡

በወንዝ ዳር በሚገኙ ሕጋዊ መጠለያዎች የሚኖሩ ወገኖችንም ለአደጋ ሳይጋለጡ ለጊዜው ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር የሚቻልበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡

በእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ይክፈለው ገ/መስቀል እንዳሉት÷ በክረምት ወቅት የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል ከጥቅምት ጀምሮ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ለጎርፍ አደጋ ስጋት ናቸው ተብለው ከተለዩ 284 ቦታዎች መካከልም በልዩ ሁኔታ አስቸኳይ መፍትሄ የሚሹ 168 ቦታዎች ተለይተው ለባለድርሻ ተቋማት ክፍፍል መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ሞገስ ባልቻ÷ 300 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የፍሳሽ ማስወገጃዎች መጸዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጽዳትና ውበት አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጀማል ጀንበሩ በበኩላቸው÷ ስለቆሻሻ አወጋገድ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እንዲፀዱ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ግንብ የመገንባት ሥራ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡

ለጎርፍ አደጋ መንስኤ የሆኑ መንገዶችን በመለየት ጥገና እንዲደረግ የማስተባበር ሥራ እየተሠራ መሆኑን የፌደራል የመንገድ ደኅንነት መድኅን ፈንድ ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች መጪውን ክረምት ተከትሎ ለጎርፍና ለትራፊክ አደጋ መነሻ የሚሆኑ የተቆፋፈሩ መንገዶችን በመቆጣጠር ጥገና እንዲደረግ እንደሚሠሩም ነው ያመላከቱት፡፡

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.