የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ክልል በበልግ እርሻ ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ማቀዱን ገለጸ

By Alemayehu Geremew

March 23, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በዘንድሮ የበልግ እርሻ ሥራ ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ክልል አቀፍ የበልግ የግብርና ሥራዎች የማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር÷ ዕቅዱን ለማሳካት ዘመናዊ አሰራር እና የግብርና ቴክኖሎጂ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል ።

ሁሉንም አካባቢዎች ወደ ተቀራራቢ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደረጃ ማምጣት እና የተቀመጠውን ግብ ማሳካት ይገባልም ብለዋል ።

የክላስተር አሰራር መከተል ፣ የግብርና ሜካናይዜሽንና ተያያዥ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምም ተገቢ መሆኑ ተገልጿል ።

ቢሮው በበልግ እርሻ 102 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ገደማ ምርት ለማምረት ማቀዱን ነው ሃላፊው የገለጹት፡፡

የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት አመራሩና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፍ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው