በህገወጥ ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመከላከል የተቋማት የተቀናጀ ስራ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገወጥ ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመከላከል የተቋማት የተቀናጀ ስራ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ፍልሰትን በጋራ ለመከላከል በተቋቋመው የብሔራዊ የፍልሰት የትብብር ጥምረት ያለፉት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
መድረኩ በህገወጥ ፍልሰተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግር መፍታትና መከላከል የሚቻልበትን ዓውድ ለማስፋት እንዲሁም ያለፉ ችግሮችን ለይቶ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ባለፉት ስድስት ወራት የማህበረሰብና የሲቪክ ማህበራትን ንቅናቄ በማሳደግ እና በዘርፉ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ የብሔራዊ የፍልሰት የትብብር ጥምረት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱ ተነስቷል፡፡
የድንበር ተሻጋሪ ፍልሰትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ላይም ኢትዮጵያ ስምምነት መፈረሟ በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።
የትብብር ጥምረቱን ሊያግዙ የሚችሉ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አህጉራዊ እና ሃገር በቀል ድርጅቶችንም የማስተባበር ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከፍልሰት አስተዳደር ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው የመንግስት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።
በይስማው አደራው