Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በደቡብ ቻይና ባህር አዲስ የጦር ሰፈር ለመገንባት ማቀዷ ቻይናን አስቆጣ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በደቡብ ቻይና ባህር አቅራቢያ አዲስ የጦር ሰፈር ለመገንባት ማቀዷ ቻይናን አስቆጥቷል፡፡

አሜሪካ በፊሊፒንስ አቅራቢያ አራት አዳዲስ የጦር ሰፈሮችን ልትገነባ መሆኑን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርከስ አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከሚገነቡት አራት የጦር ሰፈሮች ውስጥ ቢያንስ አንዱ በቻይና እና በርካታ ሀገራት የይገባኛል ጥያቄ በሚቀርብባት ደሴት አጠገብ እንደሚገነባ አረጋግጠዋል፡፡

የጦር ሰፈር ግንባታው አሜሪካና ፊሊፒንስ የመከላከያ ትብብራቸውን ለማጠናከር የተፈራረሙት ስምምነት አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ የአሜሪካ በደቡብ ቻይና ባህር ቀጣና አዲስ የጦር ሰፈር የመገንባት ዕቅድ ቻይናን ክፉኛ ማስቆጣቱ ነው የተነገረው፡፡

በተለይም አሜሪካ ሉዞ በተሰኘችው ደሴት ላይ ለመገንባት ያቀደችው የጦር ሰፈር ሀገሪቷ ከታይዋን ጋር ያላትን አላስፈላጊ ቅርበት ለማጠናከር ያለመ ነው ስትል ቻይና ትከሳለች፡፡

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዌንቢን፥ የሀገራት ወታደራዊ ትብብር የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ላይ እንጂ የሌሎችን ጥቅም ለመጉዳት ያለመ መሆን የለበትም ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ በራስ ወዳድነት መንፈስ የምታራምደው የዜሮ ድምር ጨዋታም ቀጠናውን ይበልጥ ውጥረት ውስጥ ሊከተው ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።

“የአካባቢው ሀገራትም የራሳቸውን ሉዓላዊነት በንቃት መጠበቅ እንጂ የአሜሪካ መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.