ኢትዮጵያ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚያስፈልጋት የ25 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ፋይናንስ ውስጥ በፈረንጆቹ 2019/2020 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ብቻ ማግኘቷን ጥናት አመላከተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚያስፈልጋት 25 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ፋይናንስ ውስጥ በፈረንጆቹ 2019/ 2020 1 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብቻ ማግኘቷን በዘርፉ የተሠራ ጥናት አመላከተ።
“ኤፍ.ኤስ.ዲ አፍሪካ” እና “ክላይሜት ፖሊሲ ኢኒሼቲቭ” የተባለ ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ያስጠኑት ጥናት ዛሬ ይፋ ሆኗል፡፡
ጥናቱ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2019/ 2020 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል 25 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የዓየር ንብረት ለውጥ ደጋፊ ፋይናንስ ያስፈልጋት ነበር ብሏል።
ያም ቢሆን እንደ ጥናቱ ከሆነ ሀገሪቷ ከሚያስፈልጋት የፋይናንስ መጠን 7 በመቶውን ወይም 1 ነጥብ 7 ቢሊየን የሚሆነውን ሐብት ብቻ አግኝታለች።
ይህም የ2019/20 አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን (ጂ.ዲ.ፒ) አንፃር ከ2 በመቶ በታች መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል ።
ትኩረት በተደረገበት የጥናት ዓመት ኢትዮጵያ ካገኘችው 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የዓየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ፋይናንስ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆነው ከዓለም አቀፍ የመንግስት ድጋፍ ሰጪዎች የተገኘ ነው፡፡
በሀገር ውስጥ ያሉ የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ አምራቾች ግን ለዓየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ፋይናንስ ያላቸው አበርክቶ ከ8 በመቶ እንደማይበልጥ ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ የዓየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዘላቂ የአረንጓዴ ልማትን ማከናወን የሚያስችላት የፖሊሲና የስትራቴጂ ማዕቀፍ አላት፡፡
ቢሆንም የዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለፖሊሲው ተግባራዊነት ያላቸው አበርክቶ አነስተኛ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ለአየር ንብረት ለውጡ ፋይናንስ መቀዛቀዝ በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ የሀገር ውስጥ፣ የውጭ አምራቾች እና ባለሐብቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ 56 በመቶ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስን መሳብ ላይ እና 38 በመቶ ደግሞ መቆጣጠር ላይ እንደምትሰራ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በጥናቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
በፀጋዬ ወንድወሰን