Fana: At a Speed of Life!

አቶ ጌታቸው ረዳ  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ኢፌዴሪ የፌዴሬሸን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀፅ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት፣ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግስት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማስቆም በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምት አንቀጽ (10) መሰረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም አስፈልጓል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 9 ቀን 2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብን ማጽደቁ ተመላክቷል፡፡

በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሰረት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አድርገው  መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት አስታውቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥ እና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈጻሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.