Fana: At a Speed of Life!

በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር በደብረብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
 
በማህበሩ የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዳምጠው እምሻው÷ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረብርሃን በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ወገኖች የመጠለያ፣ የአልባሳትና የምግብ ችግር እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡
 
በከተማው በስድስት መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ነው ሃላፊው የተናገሩት፡፡
 
ማህበሩ ሰሞኑን ተፈናቅለው ከመጡት ውስጥ 2 ሺህ 500 ለሚሆኑ የቤተሰብ ሃላፊዎች ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው 370 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና 1 ሺህ 225 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
 
የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ፀጋዬ በየነ በበኩላቸው÷ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቃዮች ወደ ከተማው ገብተው በህዝብ መገልገያ አዳራሾች እየኖሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
 
ወደ ከተማው የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው÷አሁን ላይ ከተማው ማስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
 
በተለይም በአንደኛው መጠለያ ጠቢያ ብቻ ከ15 ሺህ የማያንሱ ተፈናቃዮች ከደረጃ በታች ተጨናንቀው እንደሚኖሩ አመላክተዋል፡፡
 
ከዚህ በፊት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ድጋፍ ለተፈናቃዮች ያደርጉ እንደነበር ገልጸው÷ አሁን ላይ በመቆሙ ብዙዎች ለተደራራቢ ችግር መጋለጣቸውን አንስተዋል፡፡
 
በዚህ ወቅት ከእነዚህ ወገኖች ጎን መቆም የሁሉም አካላት ኃላፊነት መሆኑን አውስተው÷ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙ አካላት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.