የሀገር ውስጥ ዜና

በባሕር ዳር ከተማ በ650 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የውሃ ፕሮጀክት በግንቦት ወር አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

By Feven Bishaw

March 23, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሕር ዳር ከተማ በ650 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው የውሃ ፕሮጀክት በቀጣዩ ግንቦት ወር ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡

የከተውን የውኃ አቅርቦት ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ የ743 ሚሊየን ብር ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው÷በጃፓን መንግስት ትብብር በ650 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት በቀጣይ ግንቦት ወር ተጠናቆ አገልግሎት ይጀምራል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በከተማዋ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ እየተገነባ ሲሆን፥ የአካባቢውን የመጠጥ ውኃ ችግር ሙሉ በሙሉ የሚፈታ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከ25 እስከ 30 ዓመታት እንዲያገለግል ተጠንቶ እየተገነባ የሚገኘው የውኃ ፕሮጀክት አሁን ላይ 98 በመቶ ተጠናቋል።

ከሚያዚያ 1 ቀን ጀምሮም ተቋራጩ ለአሰሪው የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር አስረክቦ የሙከራ ስርጭቱን በመጀመር የፊታችን ግንቦት ወር ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ይበቃል ነው የተባለው።”

ከአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ውጪ ባሉ የከተማዋ ክፍሎች ያለውን የውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታትም በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ በ93 ሚሊየን ብር ወጪ ይባብ አካባቢ ከሚገኘው የጥቁር ውኃ ምንጭ ወደ ከተማው የሚያደርሰውን የ12 ኪሎ ሜትር ያረጁ ቧንቧ መስመሮችን የመቀየር ስራ ተጠናቋል ተብሏል።

የዚህ ፕሮጀክት የአፈጻጸም ደረጃ 99 በመቶ የደረሰ ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ገጠማው እንደተጠናቀቀ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገልጿል።