አቶ ሰለሞን ሶካ ከዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት የአፍሪካ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ከዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት የአፍሪካ ዳይሬክተር አነ ራቼል ኢን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎቹ በውይይታቸው÷ በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የሳይበር ደህንነትን በቅንጅት ከማስጠበቅ አኳያ ከአፍሪካ የሳይበር መከላከልና ምላሽ መስጫ ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
ኢመደአ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ኮንፍረንሶችና ኤግዚቢሽኖች ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግም በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ሶካ÷ተቋሙ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያለማቸውን ምርት እና አገልግሎቶችን እንዲሁም በኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል የሚገኙ ታዳጊዎች በተለያዩ የሳይበር ደህንነት ዘርፎች የሰሯቸውን ስራዎች ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት የአፍሪካ ዳይሬክተር አነ ራቼል ኢን በበኩላቸው÷ኢመደአ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት ከመደገፍ አንፃር የሰራቸውን ስራዎች አድንቀዋል፡፡
በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት ተቀናጅተው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ሥራዎችን እንዲሰሩ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውንም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡