ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብር ሱፐር አፕ የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብር ሱፐር አፕ የተሰኘ መተግበሪያ በሳይንስ ሙዚየም ይፋ አድርጓል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ÷ ቴሌብር ሱፐር አፕ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስረድተዋል።
የታቀደ ክፍያ፣ ለቡድን ገንዘብ መላክ፣ የዕድል ጨዋታ በቴሌብር ሱፐር አፕ መተግበሪያ የተካተቱ አዳዲስ አገልግሎቶች መሆናቸው ተገልጿል።
የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያው “እልፍ ጉዳይ በአንድ መተግበሪያ” በሚል ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ቋት ለማግኘት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
አዲሱ መተግበሪያ አሁን በሥራ ላይ ካለው የቴሌብር መተግበሪያ ጋር ተያይዞ የሚታዩ የአፈጻጸም፣ የሴኩሪቲ ሲስተም፣ ወደ ሲስተም ማስገቢያና ምዝገባ ጊዜ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በማውረድ የስልክ የዳታ የመያዝ አቅም መቀነስና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያስችላል ተብሏል፡፡
ደንበኞች አዲሱን የቴሌብር ሱፐርአፕ መተግበሪያ ለመጠቀም በቀላሉ ፕሌይ ስቶር፣ አፕ ስቶር እና አፕ ጋለሪ ላይ በመግባት፣ ነባሩን የቴሌብር መተግበሪያ አሻሽል የሚለውን በመጫን አፑን በቀላሉ አውርደው መጠቀም ይችላሉም ነው የተባለው፡፡
በአዲሱ ሙሉነህ