Fana: At a Speed of Life!

የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር የጤና ተቋማት የአገልግሎት ትስስርን ማጎልበት ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር የጤና ተቋማት የአገልግሎት ትስስርን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የጤና ስርዓት ማጠናከር እና የጤና ተቋማት አገልግሎት ትስስር በተለይ የእናቶች፣ ህጻናት ፣ አፍላ ወጣቶች እና የስነ ተዋልዶ ጤናን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት የሚያግዝ መርሐ-ግብር ማስጀመሪያ መድረክ ተካሄዷል።

በጤና ሚኒስቴር የጤና ስርዓት አቅም ግንባታ ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶክተር ደሳለኝ በቀለ ፥ በሀገር የጤና ጥራትን ለማስጠበቅና ለማጠናከር፣ የጤናው ዘርፍ እና ክብካቤ ጥራትና ደህንነት እስትራቴጂን መተግበር እና መሰረታዊ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

አክለውም ፥ ለውጥ በሚያመጡ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት ይገባልም ብለዋል።

የኢንስቲትዩት ፎር ሄልዝ ኬር ኢንፕሩቭመንት (አይ ኤች አይ) ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር አብዩ ክፍሌ በማብራሪያቸው ፥ ጥራት ተኮር የጤና ስርዓት ለእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች እንዲሁም የስነ ምግብና ስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ማሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡

በተመረጡ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና አፋር ክልል በሚገኙ ሠባት ወረዳዎችም በቀጣይ ሦስት ዓመታት የክልል ጤና ቢሮዎች ጋር ለመስራት የሚያስችለውን ድጋፍ ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ለፕሮግራሙ መተግበሪያ የተመደበለት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩት ፎር ሄልዝ ኬር ኢንፕሩቭመንት የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የጤናው ክብካቤ ጥራት እና ደህንነት እስትራቴጂዎች እና የተለያዩ ፕሮግራሞች በታቀደው ልክ መፈጸም እንዲችሉ ይሰራልም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የጤናው ዘርፍ የሰው ሀብት አቅም ግንባታ ላይ ለመስራት የጤና ስርዓቱን ማጠናከርና ማዘመን እንዲቻል በጤና ተቋማት መካከል ያሉ የጤና ስርዓቱን ማስተሳሰር ላይ ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮግራም ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.