Fana: At a Speed of Life!

ሀገር አቀፍ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሀገር አቀፍ የሕዳሴ ግድብ ቦንድ ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተጀምሯል።

የቦንድ ሳምንቱ የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የግድቡን 12ኛ ዓመት አስመልክቶ ካዛጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያ እና ሌሎች ሁነቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሃገር አቀፍ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ÷ “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ አድዋ ድል ከፍተኛ የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት ነው” ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያን ከውጪ ብድርና እርዳታ ተላቃ ነጻ ኢኮኖሚ እንድትጎናጸፍ ለማስቻል ለሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ተስፋ በማስቀጠል አንድነትን በማጠናከር በግድቡ ላይ የቀጠለውን የውጪ ጫና ማስቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ በአባይ ተፋሰስ የሚካሄዱ የአካባቢ የጥበቃ ስራዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም ለግድቡ በገንዘብና በቦንድ ግዢ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ለአንድ ወር እንደሚቆይ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የቤኑሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግራኝ ጉዳታ በበኩላቸው÷ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ከክልሉ ከ100 ሚሊየን ብር ለግድቡ ገቢ መሰብሰቡን አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በየደረጃው የሚገኙ የስራ ሃላፊዎች እና ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

ለአንድ ወር በሚቆየው መርሐ ግብር 100 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷልም ነው የተባለው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.