Fana: At a Speed of Life!

አትሌት መዲና ኢሳ ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድርን አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት መዲና ኢሳ ዛሬ የተካሄደውን ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር አሸነፈች፡፡

እንዲሁም ፅጌ ገብረ ሰላማ ሁለተኛ፣ መልክናት ውዱ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ጨርሰዋል፡፡

ለአንደኛ ደረጃ 70 ሺህ ብር፣ ለሁለተኛ ደረጃ 45 ሺህ ብር እንዲሁም ለሦስተኛ ደረጃ 30 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

የ2015 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መነሻና መድረሻውን ቦሌ አትላስ አደባባይ ያደረገ ነው፡፡

ውድደሩን ያዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሲሆን ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ ነው የተካሄደው፡፡

በውድድሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት መሰረት ደፋር እና የዓለም ሻምፒዮኗ አትሌት ለተሰንበት ግደይ እንዲሁም ሌሎች አትሌቶች እና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የማነቃቂያ መድረኮች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውድድሩን ላዘጋጁና ላስተባበሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

“ቦታዬ፤ መብቴ፤ ድምፄ” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ውድድር÷ አትሌቶች፣ 15 ሺህ የጤና ሯጮች እና አምባሳደሮች ተሳትፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.