Fana: At a Speed of Life!

የ2014 የ12ኛ ክፍል ውጤት ብዙ የቤት ሥራ እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው – አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2014 የ12ኛ ክፍል ውጤት ገና ብዙ የቤት ሥራ እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ገለጹ፡፡

በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት መቀነስ መንስኤዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የትምህርት አጀንዳ ከሁሉ በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ በመድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡

የትምህርት ተደራሽነት እና የሰው ኃይል ማሟላት ለትምህርት ጥራት መሰረት ስለሆነ÷ ዘንድሮ የተፈጠረውን ስብራት ለመጠገን ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ያጋጠመውን ዝቅተኛ የፈተና ውጤት ችግር በመቀልበስ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ እንሠራለን ብለዋል፡፡

ለዚህም በየደረጃው የሚገኘው አመራር፣ ህብረተሰቡና የትምህርት ማህበረሰቡ በቁጭት በመነሳት በትምህርቱ ዘርፍ ስኬት ለማስመዝገብ በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ተማሪዎችም የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውንና የሀገራቸውን ገጽታ ለመቀየር በትምህርታቸው ላይ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

መምህራንም ትውልድ የመገንባት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ አቶ ርስቱ አሳስበዋል፡፡
ባለፈው ውጤት በመቆዘም ጊዜ ማባካን እንደማይገባ ጠቁመው÷ አበረታች ውጤት ለማምጣት ባለድርሻ አካላት በሙሉ አቅም ወደ ስራ እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ 2 ነጥብ 6 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸው ይታወሳል፡፡

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.