የሀገር ውስጥ ዜና

በጫሞ ሐይቅ 8 ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጠመች

By Mikias Ayele

March 26, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ከአማሮ ልዩ ወረዳ አልፉጮ አቡሎ ወደ አርባምንጭ ከተማ ስምንት ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ መስጠሟን የደቡብ ክልል ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ፥ ጀልባዋ ስምንት ሰዎች አሳፍራ ትጓዝ እንደነበር አረጋግጠዋል።

የአደጋው መንስኤ ከመጠን በላይ መጫን ሳይሆን እንዳልቀረ ጠቁመዋል።

እንዲሁም በወቅቱ ባልተለመደ ሁኔታ የተከሰተ ማዕበል መኖሩም ተመላክቷል።

ጀልባዋ ከሥምንቱ ሰዎች በተጨማሪ ከ60 ኩንታል በላይ ዕቃ መጫኗን የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደግፌ ደበላ ገልፀዋል።

የሕይወት አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው ፥ ለዚህም የተለያዩ ጀልባዎችና ዋናተኞች ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።

በተከናወነው የፍለጋ ሥራ ከጫማዎች እና የተለያዩ አልባሳት ባለፈ የተገኘ ነገር የለም ብለዋል።

ሥድስቱ ተሳፋሪዎች ሲሆኑ ሁለቱ ቀዛፊውና ረዳቱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የአማሮ ልዩ ወረዳ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብሩክ አየለ እንዳሉት ፥ የመስጠም አደጋው ትናንት ከሰዓት ነው ያጋጠመው።

የሥራ ኃላፊዎቹ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እስካሁን በሕይወት የተገኘ አለመኖሩን ጠቁመው፥ ተሳፋሪዎችን ከዚህ በኋላ በሕይወት የማግኘት ተስፋው መሟጠጡን ተናግረዋል።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!