Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የውክልና ስራው ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የሕዝብ ድምፅ እንዲሰማ ይሰራል- አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ ከተሰጡት ተግባራት አንዱ የሆነውን የውክልና ስራ የሕዝብ ድምፅ እንዲሰማ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ያሰባሰቧቸውን የተለያዩ የሕዝብ ጥያቄዎች ለአስፈፃሚ አካላት ከፍተኛ አመራሮች አቅርበው ውይይት ተደርጓል፡፡

አፈ ጉባዔ  ታገሰ ጫፎ የምክር ቤቱ አባላት ባለፈው የካቲት ወር ከመራጩ ህብረተሰብ ጋር ተወያይተው ከሕዝቡ የተነሱ አንኳር ጥያቄዎችን ይዘው ከተለያዩ አስፈጻሚ አካላት ጋር በየደረጃው ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎች በተገቢው ተለይተው  ምላሽ ሊያገኙ ስለሚገባ የዛሬው ውይይት ከፌደራል አስፈጻሚ አካላት ጋር ባለው ግንኙነት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጅጌ÷ ምክር ቤቱ በሚሰራቸው የውክልና ስራዎች የሕዝብን ድምጽ በመስማት ለሕዝቡ የገባውን ቃል ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሕዝቡን ጥያቄ ተቋሟዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ መድረክ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በሁሉም ዘርፎች አበረታች ለውጦች ስለመኖራቸው፣ ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥም ቢሆን ከፍተኛ ስኬቶችን እያስመዘገበች መሆኗን፣ የሕዝብ ውክልና ስራን በአግባቡ በመሥራት፣ የተጠያቂነት ሥርዓት በማጠናከር ምክር ቤቱ ከሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ  ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም የሰላም ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ ለአስፈጻሚ አካላት ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት÷ በሕዝብ ውክልና ሥራ ላይ በስፋት የተነሱና በአስፈጻሚ ተቋማትም በትኩረት ተይዘው ሊሰሩ ይገባሉ የተባሉ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በየካቲት ወር ባደረጉት የመራጭና ተመራጭ መድረክ በሀገር አቅፍ ደረጃ በአምስት ክልሎች፣ በ41 ዞኖች፣ በ950 ወረዳዎች እና በ645 ቀበሌዎች ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም 39 የሚደርሱ ተቋማት ተለይተው መቅረባቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሪፖርቱ በስፋት እንደ ችግር ከተነሱት ጉዳዮች የሰላምን ዕጦት፣ የፍትህ ስርዓት የአተገባበር ችግር፣ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጉድለት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም ስራ አጥነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተነሱ ጉዳዮች ላይ የአስፈፃሚ አካላት አመራሮች ምላሽ የሰጡ ሲሆን÷ በተለይ ትኩረት የተሰጠባቸው የመንገድ፣ የመብራት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የጤና ተደራሽነት፣ የትምህርት ጥራት፣ የሰላም እና ደህንነት እንዲሁም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ የማቋቋም ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ተሠጥቷል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.