Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በማኅበረሰብ-አቀፍ የበግና ፍየል ዝርያ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ተጠቃሚ ሆናለች ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የገጠሩ ክፍል በአነስተኛ የግብርና ሥራ እና እንስሳት በማርባት የሚተዳደረውን የማኅበረሰብ ክፍል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የእንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት ገለጸ፡፡

በተለይም በግ እና ፍየል በማርባት የሚተዳደረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢፌዴሪ የእንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት ዘር የማሻሻል መርሐ-ግብር ከጀመረበት ከፈረንጆቹ 2007 ጀምሮ ተጠቃሚ መሆኑን የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና ተመራማሪ አሥራት ጤራ ገልጸዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአዳጊ ሀገራት ደረቃማ አካባቢዎች የሚተገበሩ የግብርና ሥራዎችን ምርታማነት እና ጥራት በምርምር ለማሻሻል ከሚሰራው የዓለም አቀፉ ደረቃማ አካባቢዎች የግብርና ምርምር ማዕከል ውስጥ ተመራማሪዎች ከሆኑት ተስፋዬ ጌታቸው እና ዓይናለም ኃይሌ ጋር ቆይታ ነበረው፡፡

ማዕከሉ ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ ከኢፌዴሪ የእንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት፣ ከኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ፣ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከምርምር ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር አርቢውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ተመራማሪዎቹ አስረድተዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ዋና ዋና የበግና ፍየል ዝርያዎችን ሙሉ በሙሉ በሀገሪቷ ለማስፋት እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች 146 ያህል ማኅበረሰብ ዓቀፍ የበግ እና የፍየል ዝርያ ማሻሻያ መርሐ-ግብሮች እየተከናወነ መሆኑን ተመራማሪው ተስፋዬ ጌታቸው አንስተዋል፡፡

የዝርያ ማሻሻያ መርሐ- ግብሩ ማኅበረሰብ-አቀፍ የእንስሳት እርባታ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማቋቋም ፣ የምርት አቅርቦት ተረካቢዎችን እንዲሁም በማድለብ ላይ የሚሠማሩ ኢንተርፕራይዞችን በማስተሳሰርና ጥራት ያለው የሥጋ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየሰራ እንደሆነም ተገጿል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዋሸራ በግ ዝርያ ላይ 28 ማኅበረሰብ-አቀፍ መርሐ-ግብሮች ሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን፥ እነዚህም በየአመቱ 8 ሺህ ያህል ምርጥ አውራዎችን የማምረት አቅም እንደሚኖራቸውም ነው የተገለጸው።

ከዚህ ባለፈም በጋራ መስራት ከተቻለ ምርጥ ዝርያዎቹን 70 ሺህ ለሚሆኑ ቤተሰቦች በማሰራጨት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ደረቃማ አካባቢዎች የግብርና ምርምር ማዕከል ከአጋራ አካላት ጋር በመሆን የበግና ፍየል ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዙ በርካታ የመኖ ልማትና ማድለብ፣ የጤና አጠባበቅ እና የገበያ ትስስር ቴክኖሎጅዎች ለተጠቃሚዎች ዝግጁ መሆናቸውን አይናለም ኃይሌ የማዕከሉ ዋና ተመራማሪ አስታውቀዋል።

በዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.