Fana: At a Speed of Life!

እስካሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች 282 ሺህ 934 ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ተሰራጭቷል -ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ካለፈው ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች 282 ሺህ 934 ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ መሰራጨቱን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
 
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በግጭት ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚሰራጨው የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
 
አሁን ላይ በትግራይ ክልል ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ፣ በአማራ ክልል ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ እና በአፋር ክልል ደግሞ ከ715 ሺህ በላይ በአጠቃላይ ከ8 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ እርዳታ ፈላጊ ዜጎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
 
ተረጂዎቹ በትግራይ ክልል ሁሉም ዞኖች፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች እንዲሁም በአፋር ክልል ዞን ሁለት፣ አራት እና አምስት የሚገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ለእነዚህ ዜጎች በመጀመሪያ ዙር 141 ሺህ 671 ሜትሪክ ቶን በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ መሰራጨቱን ነው የተናገሩት፡፡
 
የ2ኛውን ዙር ጨምሮም እስካሁን ለሶስቱ ክልሎች 282 ሺህ 934 ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ መሰራጨቱን አቶ ደበበ ጠቅሰዋል፡፡
 
መንግስት 15 ሺህ 666 ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረቡን ያነሱት ዳይሬክተሩ ÷ሌላው ድጋፍ ደግሞ በአጋር አካላት የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ለእናቶች፣ ህጻናት፣ ነፍሰጡር እናቶች እና አዛውንቶች ደግሞ 5 ሺህ 938 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግብ ተደራሽ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
 
እስካሁን በትግራይ ክልል ለአስተዳደራዊ ጉዳች እና ለአገልግሎት ማስፈጸሚያ የሚውል 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ወደ መቀሌ እና ሽረ መላኩን ተናግረዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.