የነርቭ እና የእድገት እክል (ኦቲዝም) ምንድን ነው ?
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነርቭ እና የእድገት እክል (ኦቲዝምእስፔክትረም ዲስ ኦርደር) ማለት ከነርቭና አንጎል አሰራር ሒደት ጋር ግንኙነት ያለው የእድገት እክል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
እስፔክትረም ማለት የእክሉን ደረጃ፣ መጠን፣ የምልክቱን ልዩነት ጠቅልሎ የያዘ አጠራር እንደሆነ ነው የሚገልጹት፡፡
አንዳንድ ምሁራን “ኦቲዝም እስፔክትረም ዲስ ኦርደር” የሚለውን ትርጓሜ ወደ አማረኛ ሲቀይሩት የህብረ-ባህሪ የአዕምሮ እድገት መዛባት እንዲሁም የነርቭ እና የአንጎል ስርዓት እድገት እክል ነው ይላሉ፡፡
ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ተግባራትን ከሌሎች ሰዎች በተለየ መንገድ ሊፈጽሙ ይችላሉ፤ ከማህበረሰቡ ጋር የሚግባቡበት መንገድ እና የሚማሩበት ሒደትም በተለየ መንገድ ሊሆን እንደሚችልም ይገለጻል፡፡
“ኦቲዝም “በማንኛውም የእድሜ ክልል ሊታወቅ ቢችልም በአብዛኘው ጊዜ ግን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ምልክቶች የመታየት እድል ይኖራቸዋል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡
ከፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የስነ-ልቦና ባለሙያው ምናለ ሽባባው÷ ከህጻናት የነርቭ እና የእድገት መታወክ ጋር በተያያዘ ለመምህራን እና እክሉ ላለባቸው ህጻናት የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡
በዚህ እክል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጠቅለል ባለ መልኩ ሶስት መሰረታዊ ችግሮች እንደሚታዩባቸው ነው የስነ-ልቦና ባለሙያው ያስረዱት፡፡
እነርሱም÷የተግባቦት ችግር፣ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለመመስረት መቸገር እንዲሁም ውስን የሆኑ ባህሪያትንና ጸባያትን በተደጋጋሚ ማሳየት ናቸው ይላሉ፡፡
በአብዛኛው እክሉ ያለባቸው ልጆች ከሚሳዩዋቸው ምልክቶች መካከል÷ ፊት ለፊት ሰዎች ጋር የመተያያት ችግር ፣መናገር አለመቻል ወይም መዘግየት፣ ለስማቸው ምላሽ አለመስጠት፣ ራሳቸውን ማግለል፣ ስሜታቸውን እና ሃሳባቸውን የመግለጽ ችግር፣ ከሰዎች ጋር በሚያደርጉት ተግባቦት ንቁ ያለመሆን ወይም ቁጡ መሆን የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ ችግሮች ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ ህይዎታቸውን እንዳይመሩ እንቅፋት እንደሚፈጥርባቸውም ባለሙያው ያነሳሉ፡፡
“ኦቲዝም” ህመም ወይምበሽታ ስላልሆነ ለተወሰነ ጊዜ በሚወሰድ መድሃኒትና ህክምና የሚድን ሳይሆን እክሉ ከደረሰበት ሰው ጋር ለረጅም አድሜ የሚቆይ ፣ተገቢ የሆነ ትምህርት ስልጠና እና ክትትል ከልጅነት እድሜ ጀምሮ ከተደረገ ብዙ መሻሻሎችን ማምጣት እንደሚችልም ይናገራሉ፡፡
ባለሙያው “ኦቲዝም” ያለባቸውን ልጆች እንዴት ማሰልጠን እንደሚቻል ሲያስረዱ በሶስት ዋናዋና ነጥቦች ስር ያጠቃልሏቸዋል፡፡
እነርሱም÷ማስተካከል እና ማስለመድ የምንፈልገውን ጸባይ መለየት፣ግብ ወይም አላማ ሰናስቀምጥ፣ እኛ በፈለግነው መጠን ወይም ልክ ሳይሆን የልጆችን አቅም እና ተሰጥኦ ባገናዘበ መልኩ ቢሆን የሚሉት እና እክሉ ያለበት ልጅ የሚወደውን ነገር መለየት የሚሉት ዋነኞቹ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
ችግሩ ያለበትን ሰውን ቤተሰብ ወይም አሳዳጊ በመጠየቅ እና ተከታታይ ግምገማ ወይም ምልከታ በማድረግ መለየት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡
የልጆችን አቅም እና ደረጃ በደንብ በማጥናት ወይም ግምገማ በማድረግ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ በማሰልጠን ተገቢ በሆነ መልኩ ማብቃት እንደሚቻልም ይገልጻሉ፡፡
የነርቭ እና የእድገት መታወክ ያለባቸውን ልጆች ተገቢውን ክትትል እና ስልጠና በሰጠናቸው መጠን ለውጥ የሚያመጡ ሲሆን÷ ለእኛ ግን ለውጡ ፈጣን ትርጉም ያለው ላይመስል እንደሚችልም ባለሙያው አንስተዋል፡፡
ይህም የሚሆነው ለውጡን በራሳችን መንገድ ስለምናየው እንጂ ለነሱ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ተረድተን ተከታታይ ስልጠና በመስጠት በሚገባ ማብቃት ይቻላል ይላሉ።
ለውጡን ባለመረዳት በፍጥነት ከአቅማቸው በላይ ለማሰልጠን መሞከር በልጆች ላይ ከባድ ጫና በመፍጠር እና ከባድ ውጥረት ውስጥ በማስገባት ለሚሰጣቸው ተከታታይ ስልጠና እና እገዛ ያላቸውን ፍላጎት እንዲቀንስ በማድረግ ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ሊያደርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ስለዚህ÷ ግብ ወይም አላማ ሰናስቀምጥ እኛ በፈለግነው መጠን ወይም ልክ ሳይሆን የልጆችን አቅም ፣ተሰጥኦ ባገናዘበ መልኩ መሆን እንዳለበት ነው ባለሙያው የሚያስረዱት፡፡
የሚፈልጉትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ወይም ወደ ሚፈልጉት ቦታ በመወሰድ በሚፈልጉትን እቃ፣ መጫዎቻ፣ በማቅረብ የምንፈልገውን ጸባይ ለመልመድ ሲሞክሩ ማበረታቻ በመስጠት ማሰልጠን ዋና አማራጭ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!